ቀጥታ፡

የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማተራመስ አጀንዳና የውጭ አገራትን ጣልቃ ገብነት አጥብቀን እናወግዛለን - አስተያየት ሰጪዎች

ጥቅምት 12/2015(ኢዜአ) የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማተራመስ አጀንዳና የውጭ አገራትን ጣልቃ ገብነት አጥብቀን እናወግዛለን ሲሉ በአዲስ አበባ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የተገኙ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን የሚያወግዝና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባና ዛሬ ማለዳ በመላው አገሪቱ ''ለኢትዮጵያ  እቆማለሁ  ድምጼንም  አሰማለሁ'' በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።

በሰልፉ ላይ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተለያዩ  ሃይማኖት የተውጣጡ አባቶችና እናቶች ማልደው ለአገራቸው ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በሰልፉ ላይ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት፤  ሁሉም  በሰላም  ወጥቶ  የሚገባው  ሰላም  ሲኖር ነው፣  ሀይማኖትና  ስርዓት  ባህል ወግ  የሚከበረውም  አገር  ስትኖር ነው።

በመሆኑም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር  በማበር  በአገሪቱ  ሰላምና  አንድነት  እንዳይኖር የሚያደርጉ ሁሉ ከድርጊታቸው  እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

መንግስት ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ መስጠቱ የሚደነቅ መሆኑን በመጥቀስ ህዝቡን ለእንግልትና ለስቃይ የሚዳርጉትን አጥበቀው እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት የቆየ ልምድና  ስርዓት ስላላት  የውስጥ  ጉዳችንን  በራሳችን እንድንፈታ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለኢትዮጵያዊያን ተዉልን ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ፈላጊ በመሆኑ ይህ ጦርነት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማቱ እንዲዞር አሁንም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም