"የአሸባሪው ህወሃት የተሳሳተ ትርክት እየጠፋ በመምጣቱ በህዝቦች መካከል አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር እያበበ መጥቷል"-አርቲስት ጸጋዬ ደንደና - ኢዜአ አማርኛ
"የአሸባሪው ህወሃት የተሳሳተ ትርክት እየጠፋ በመምጣቱ በህዝቦች መካከል አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር እያበበ መጥቷል"-አርቲስት ጸጋዬ ደንደና
አዳማ ጥቅምት 12/2015 (ኢዜአ) "የአሸባሪው የህወሃት ጁንታ የተሳሳተ ትርክት እየጠፋ በመምጣቱ በህዝቦች መካከል አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር እያበበ መጥቷል" ሲል አርቲስት ፀጋዬ ደንደና ተናገረ።
አርቲስት ጸጋዬ ይህን አስተያየት የሰጠው "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ" በሚል መሪ ቃል የአዳማ ከተማና የምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በተሳተፉበት ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ በተሳተፈበት ወቅት ነው።
በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።
አሸባሪው ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የሀገርና የሕዝብ ሀብትን ከመዝረፍ ባሻገር ወንድማማች ህዝቦችን በሴራ ሲያከፋፈልና ሲያጋጭ ነበር ሲሉ በህዝባዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት የምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
አርቲስት ጸጋዬ ደንደናም በዚሁ ጊዜ እንደተናገረው ''ሰልፉ ላይ የታደምኩት ድምፄን ለማሰማት ብቻ ሳይሆን አሸባሪውን ለማጥፋት የሚደረገውን ትግል ለማገዝ ነው'' ብሏል።
የአደአ ወረዳ ነዋሪ አቶ ለሜቻ ቡታ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን የህዝብና የመንግሥትን ሀብት ሲዘርፍ ነበር ብለዋል።
ከዚህም አልፎ ወንድማማች ህዝቦችን በሴራ በማጋጨት ሀገር እንድትፈርስ ሲሰራ የነበረ ቡድን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አሸባሪው ህውሃት ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ህይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድምና በወንድማማቾች መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር በማድረግ ኢትዮጵያን ለመበተን ከጅምሩ አልሞ የተነሳ ቡድን መሆኑንም ተናግረዋል።
በአሸባሪው ህወሃት የውሸት ፕሮፓጋንዳ ተታለው በሀገራችን ላይ ያልተገባ ተፅዕኖ እና ጫና የሚፈጥሩ አካላትን አጥብቀን እንቃወማለን ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
የዱግዳ ወረዳ ነዋሪው አቶ በዳሶ ፈቱላ በበኩላቸው ሁሉም ህዝብ አንድ ሆኖ ከመንግሥትና ከመከላከያ ጎን በመሆን ሽብርተኞችን መከላከል አለበት ብለዋል።
በህዝባዊ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት የሆኑት ወታደር ይታገሱ እና ሻምበል መኮንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንትም ቢሆን በሉዓላዊነቱና በአገሩ ጉዳይ ከማንም ጋር እንደማይደራደር በተግባር ያስመሰከረ ነው ብለዋል።
''ማንም ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት አይችልም፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ አንደራደርም'' ብለዋል የቀድሞ የሰራዊት አባላቱ።