ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን ጣልቃ ገብነትን እንደማይቀበሉ ግልጽ መልዕክታቸውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስተላልፈዋል - ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ

ጥቅምት 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያውያን በዛሬው ሰልፍ ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል” ስትል ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ተናገረች።

“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ አሸባሪው ሕወሓትን የሚያወግዝና የአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ ሰልፎች ዛሬ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተካሂደዋል።

ሰልፉ ጊዜውን የጠበቀና ኢትዮጵያውያን ጣልቃ ገብነትና ጫና እንደማይቀበሉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ መልዕክት የተላለፈበት እንደሆነ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ገልጻለች።

ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር የትኛውንም አይነት ዋጋ እንደሚከፍሉ እንዳሳዩም ጠቅሳለች።

“የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሩ፣ ጣልቃ ገብነትን አንቀበልም፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁምና በአንድ ሉዓላዊ አገር ሁለት ሰራዊት አይኖርም” የሚሉ መፈክሮች በሰልፎቹ ላይ ጎልተው መሰማታቸውን ተናግራለች።

በአዲስ አበባና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በተካሄዱት ሰልፎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መሳተፉን ተረድቻለሁ ያለችው ጋዜጠኛዋ፤ ኢትዮጵያውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሰማት የጀመሩትን ድምጽ ማስቀጠል እንደሚገባቸው አመልክታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም