ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባትና አንድነታችንን ለመናድ የሚጥሩ አንዳንድ ምዕራባውያንን በጋራ መመከት አለብን-አስተያየት ሰጪዎች

ጥቅምት 12/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባትና አንድነታችንን ለመናድ የሚጥሩ አንዳንድ ምዕራባውያንን በጋራ መመከት እንደሚገባ በአዲስ አበባ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ገለጹ።

"ለኢትዮጵያ ዘብ እቆማለሁ ድምጼንም አሰማለሁ' በሚል መሪ ዐሳብ አሸባሪውን ህወሓት የሚያወግዝ እና የምዕራባዊያንን  ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ህዝባዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በዛሬው እለት ተካሂዷል።

በህዝባዊ ሰልፉ የህወሓትን የሽብር ቡድን ዕድሜ ማራዘም ይብቃ፣ በሉዓላዊነታችን አንደራደርም፣ በውክልና ጦርነት መጠቃት ይብቃን የሚሉ መፈክሮች በስፋት ተሰምተዋል።

በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም የሚሉ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዙ መፈክሮችም ተስተጋብተዋል።

በህዝባዊ ሰልፉ ላይ ያገኘናቸው ብርሀኔ ዘውዴ የአንዳንድ ምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት በአንድነት መመከት ይገባል ብለዋል።

የተላላኪዎቻቸውን ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያን ማስቀጠልና ጠላቶቿን እስከወዲያኛው መፋለም እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

አንዳንድ ምዕራባውያን  በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባትና አንድነታችንን ለመሸርሸር የሚያደርጉትን ሙከራ ሊያቆሙ ይገባልም ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ቢያድግልኝ ወርቄ ለአገር ሉአላዊነት መከበር አንድነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ነጻነቷንና ክብሯን ጠብቃ ለዘመናት የኖረች እንደመሆኗ ለመከፋፈል የሚሞክሩ አካላትን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ወጣት ጅላሉ ዘይኑ በበኩሉ እንደተናገረው የኢትዮጵያ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገራቸው ዘብ መቆም የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው።

ቀደምት ኢትዮጵያወያን ሀገርን አንድ አድርገው እንዳስረከቡን  ሁሉ ወጣቶችም ይህንን ገድል ልንደግመው ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም