በፓርኮችና መጠለያዎች የሚታዩ ችግሮችን ይፈታል የተባለ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በፓርኮችና መጠለያዎች የሚታዩ ችግሮችን ይፈታል የተባለ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮችና መጠለያዎች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል የተባለ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ። በረቂቅ ፍኖተ ካርታው ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት ውይይት በደቡብ ክልል ጂንካ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው። በኢትዮጵያ የሚገኙት 27 ብሄራዊ ፓርኮች መካከል አብዛኛዎቹ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ህልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል። ህገ-ወጥ የእርሻ መስፋፋት፣ የመሬት ወረራ፣ ሰፈራ፣ የማዕድን ቁፋሮ፣ ልቅ ግጦሽ እና በዱር እንስሳቱ ላይ የሚካሄደው ህገ-ወጥ አደን ፓርኮቹን ለጥፋት ከዳረጓቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ችግሮቹን በመፍታት የፓርኮቹን ህልውና ለማቆየት ምጣኔ ኃብታዊና ስነ-ምህዳራዊ ፋይዳቸውን ለማጎልበት እስካሁን የተደረጉት ጥረቶችም የታለመውን ግብ መምታት አልቻሉም። የፓርክ ልማትና ጥበቃን በተመለከተ የማህበረሰቡ ግንዛቤ እና የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነት አናሳ መሆን ከዘርፉ ጋር በተያያዘ ለሚታዩት ፈተናዎች ለመፍታት እንዳላስቻለ ተነግሯል። እንደዚሁም በፓርኮቹ አቅራቢያ የሚኖረው ማህበረሰብ ህይወት በዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢዎች ላይ ጥገኛ መሆን፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች በሰው ሰራሽ ጫና ሥር መውደቃቸው ሌሎቹ ችግሮች እንደሆኑም ይገልፃል። በውይይቱ ላይ እንደተገለፀው ፍኖተ ካርታው በዱር እንስሳት ጥበቃ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የሚፈቱበትን ስልት የሚቀይስ ነው። በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ፋኑኤል ከበደ እንደሚሉት፤ ፍኖተ ካርታው የዱር እንስሳት ዝርያ ጥበቃን ለማጎልበት፤ ህልውናቸው ለአደጋ የተጋለጡትን ደግሞ ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው። ይህንንም እውን ማድረግ ይቻል ዘንድ በፓርኮቹ አካባቢ የሚኖረውን ህብረተሰብ በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን አማራጭ ሃብት ማጎልበትም የፍኖተ ካርታው ግብ ነው። የተቀናጀና የተሟላ ምርምር በማድረግ የዘርፉን ልማት ማጠናከር እንዲሁም ለፓርኮቹ አደጋ የሚሆኑ መጤ የእፅዋት ዝርያዎችን መከላከልም በፍኖተ ካርታው ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ዶክተር ፋኑኤል ገልፀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመገናኛ ባህልና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ ወይዘሮ ሙሂጅብ አብዱ እንደናገሩት፤ የፍኖተ ካርታው መዘጋጀት ዘርፈ ብዙ የሆነውን የብሔራዊ ፓርኮችና መጠለያዎች ችግርን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ያስችላል፡፡ ይሁንና ፍኖተ ካርታው ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር ውይይትና መግባባት እንዲደረግበት አሳስበዋል። ፍኖተ ካርታው በተሻለ መጠን ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላትን በተለይም ደግሞ የምሁራንን ግብዓት በበቂ ሁኔታ ማካተት እንደሚጠበቅበትም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት ለፓርኮቹ ህልውና አደጋ ናቸው የተባሉትን ችግሮች ለመለየት የተደረገውን ጥረት የጠቀሱት ተወካይዋ የሌሎች አገሮችን ልምድና ተሞክሮ መመልከትም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በፓርኮች አካባቢ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ፍኖተ ካርታው ላይ በሚካሄዱ ውይይቶች የሚገኙትን ግብኣቶች በማካተት በአፋጣኝ ወደ ተግባር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በፓርኮቹ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለመመለስ የሚያስችል አሰራርም ይዘረጋል ተብሏል። የየፓርኩ ተቀጣሪ ሠራተኞችን መብት ጥበቃና ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲሁም ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግም ፍኖተ ካርታው ያግዛል ሲሉ አክለዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከተለያዩ በዘርፉ ከሚሠሩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ ከ150 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡