ቀጥታ፡

"የእናት አገራችን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን" የሮቤ፣ አምቦና ሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ጣልቃ ገብነት የሚያወግዙ ሕዝባዊ ሰልፎች ተካሄዱ

ሮቤ፣ አምቦና ሻሸመኔ ጥቅምት 12/2015 (ኢዜአ) "የእናት አገራችን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉ የሮቤ፣ አምቦና ሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
"ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምፄን አሰማለሁ" በሚል መሪ ቃል የአሸባሪውን ህወሓት ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማና የአንዳንድ ምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዙ ሕዝባዊ ሰልፎች በየከተሞቹ ተካሂደዋል።

ከባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በሮቤ ከተማ አሸባሪው ህወሓትን በማውገዝ እና የአንዳንድ ምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

ሰልፈኞቹ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጹ፣ አሸባሪውን ህወሓትና አንዳንድ የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ እየፈጸሙት ያለውን ያልተገባ ጫና የሚያወግዙ መልዕክቶች አሰምተዋል።

መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት እንደሚደግፉና ከጎኑ ሆነው የድርሻቸውን እንደሚወጡ  ገልጸዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የአፋርና የአማራ ክልሎችን በእብሪት ወሮ በሴቶችና ህጻናት ላይ የፈጸመው አስነዋሪ ተግባር የቡድኑን የጭካኔ ጥግ እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

እንዲሁም ለትግራይ ክልል ሕዝብ ቅንጣት ታህል ርህራሄ የሌለው ህጻናትን፣ ሴቶችና አዛውንቶች በከፈተው ጦርነት ከፊት እንዲሰለፉ በማድረግ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

አንዳንድ ምዕራባውያን ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን ዕድሜ ለማራዘም እያደረጉት ያለውን ድጋፍ በፅኑ አውግዘው፤ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ከምዕራብ ሸዋ ዞን ሕዝብ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴና ያልተገባ ጫና በመቃወም በአምቦ ከተማ ሕዝባዊ ስልፍ አካሂደዋል።

የዞኑ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ!" በሚል መሪ ቃል አሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባርና የውጭ ሀይሎችን ጣልቃ ገብነት እያወገዘ ይገኛል።

ሰልፈኞቹ "ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ጣልቃ ገብነት እንቃወማለን! ሸኔ የኦሮሞ ጠላት ነው፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን እንደግፋለን፤ የሚሉ መልዕክቶችን የያዙ መፈክሮችን" እያስተጋቡ ነው።

በተመሳሳይ ዜና የምዕራብ አርሲ ዞንና የቢሻን ጉራቻ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች አሸባሪው ህወሓትን እኩይ ተግባር በማውገዝ የውጭ ሀይሎችን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በሻሸመኔ ከተማ ሰልፍ እየተካሄደው ነው።

ሰልፈኞቹ ህወሓት የትግራይን ህዝብ አይወክልም፤ የትግራይ ክልል ሕዝብ የለውጡ ተካፋይ ሊሆን ይገባል፣ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው የሚሉ መፈክሮችን እያስተጋቡ ይገኛሉ።

አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ በሀገርና በሕዝብ ላይ ግፍና በደል እየፈጸሙ ያሉ ጠላቶች በመሆናቸው ከመንግሥት ጎን ሆነን በፅኑ እንታገላቸዋለን የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ በንፁሃን ላይ እየፈጸሙ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አውግዘው ለጀግናው ሀገር መከላኪያ ሠራዊት በሁሉም መስክ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

መንግሥት የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነትና ሕልውና ለማስጠበቅና ለማስከበር እየወሰደ ያለውን የመከላከል እርምጃ እንደሚደግፉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም