በሆሳዕና፣ ጂንካ እና ዲላ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በሆሳዕና፣ ጂንካ እና ዲላ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ናቸው

ሆሳዕና፣ ጂንካ እና ዲላ (ኢዜአ) ጥቅምት 12 /2015 በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና በመቃወም “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል በሆሳዕና፣ በጂንካ እና ዲላ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።
በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ መነሻውን ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ አደባባይ ባደረገው ህዝባዊ ሰልፍ ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ በክብር ተመላሽ ሠራዊቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ሰልፈኞቹ አንዳንድ ምዕራባዊያን ለአሸባሪው ቡድን እያሳዩት ያለውን ውግንና እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ በድምጽና በመፈክር ጠይቀዋል።
መዳረሻውን በሆሳዕና ከተማ በሚገኘው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ እስታዲየም ባደረገው ሰልፍ ተሳታፊዎቹ አንዳንድ የውጭ ሀይሎች የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እንዲሁም አሸባሪውን ህወሓት እያወገዙ ነው።
ከእዚህ በተጨማሪ ውድ ህይወቱን ለሀገርና ለህዝብ ሲል እየከፈለ ላለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ሰልፈኞቹ እየገለጹ ነው።
በሰልፉ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችም በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በተመሳሳይ የአንዳንድ የውጭ ሀገራት ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም እና የህወሓትን የሽብር ድርጊት የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በሰልፉ ላይ በጂንካ ከተማ ከሰባት ቀበሌያት የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ በጂንካ ሁለገብ ስታዲየም ተሰባስበው ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
"ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ሰልፍ ህዝቡ የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት ድርጊት ከማውገዝ ባለፈ የውጭ ጣልቃገብነቱ እንዲቆም ጠይቋል።
በሰልፉ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ሲሆን “አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና ተቋማት ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ!” የሚልና መሰል መልዕክቶች በማስተላለፍ ላይ ናቸው።

በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ሰልፍ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በዲላ ከተማ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ሰልፍም የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች የውጭ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እና አሸባሪውን ህወሓት በማውገዝ ላይ ናቸው።
ነዋሪዎቹ “ለኢትዮጵያ እቆማለው፤ ድምጼን አሰማለው“ በሚል መሪ ቃል የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
በሰልፉ ላይ ከጌዴኦ ዞን 13 መዋቅሮች የተወጣጡ አካላት እንዲሁም የዲላ እና አካባቢው ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው።
በሰልፉ የተገኙት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ አሸባሪው ህወሓት በሰልጣን ዘመኑም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያን ለማዋረድ ከውጭ ደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ተግቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
"አሁንም ለ3ኛ ጊዜ ጦርነት በማካሄድ ለሰላም ቦታ እንደማይሰጥ በግላጭ አሳይቷል" ብሏል።
የሽብር ቡድኑ በሀገርና በህዝብ ላይ ጥፋት እየፈጸመ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ድርጊቱን በግልጽ ከማውገዝ ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና በማድረግ ቡዱኑን ከሞት አፋፍ ለመታደግ እየጣሩ መሆኑን አስረድተዋል።
የዞኑ ህዝብና መንግስት ያልተገባ የውጭ ጫናን አምርሮ ከመቃወም ባለፈ መንግስት የሀገር ሰላምና ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
በዲላ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ ላይ "የምዕራባዊያን ሀገራት ያልተገባ ጫናን እቃወማለው!" ፣ "በሰብአዊ እርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም!" ፣ "የትግራይ ህዝብ ወንድማችን፤ ህወሓት ጠላታችን ነው!" ፣ "ህወሓት አሸባሪ ድርጅት እንጂ ሀገር አይደለም!" የሚሉና ሌሎች መፈክሮች እየተስተጋቡ ነው።