ኢትዮጵያ የአፍሪካ አይበግሬነት ተምሳሌት ናት - አቶ ጃንጥራር አባይ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አይበግሬነት ተምሳሌት ናት - አቶ ጃንጥራር አባይ
ጥቅምት 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ የአፍሪካ አይበግሬነት ተምሳሌትና የቅኝ ገዢዎችን ሕልምን ያመከነች አገር ናት” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሉዓላዊነት አሳልፈው አይሰጡም ብለዋል።
“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ አሸባሪውን ሕወሓት የሚያወግዝ እና የምዕራባውያንን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ ዛሬ ማለዳ በመስቀል አደባባይ ተካሄዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ኢትዮጵያ በልጆቿ ተከብራ እዚህ እንደደረሰች ሁሉ ዛሬም ተከብራ ትቀጥላለች ብለዋል።
የኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋት የሚጥሩ አካላት ሁሉ እጆቻቸውን መሰብሰብ አለባቸው ፤ ኢትዮጵያን ከዕለት ፍጆታ ይልቅ ለክብራቸው ቦታ ይሰጣሉ ነገም ለክብራችን ትልቅ ቦታ እንሰጣለን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው።
አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ካልመራው ትፍረስ ብሎ ሶሰተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱን ገልፀው፤ ኢትዮጵያን በጋራ በመሆን አገራቸውን ለማዳን የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት እየመከቱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
“ተላላኪ በመሆን ኢትዮጵያን የምታስጠቁ ሁሉ አገር የሌለው ክብር የለውም ኢትዮጵያን አታድሙ” ብለዋል ምክትል ከንቲባው።
ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሉዓላዊነት መቼም አሳልፈው አይሰጡም፤ ሉዓላዊነታችንና የግዛት አንድነታችንን በጋራ ማስከበራችንን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አይበግሬነት ተምሳሌትና የቅኝ ገዢዎችን ሕልምን ያመከነች የነጻነት ተምሳሌት የሆነቸ አገር መሆኗን ሁሉም ሊያውቀው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እንድታስከብር ከጎኗ የቆማችሁ ሁሉ ክብር ይገባችኋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሕዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀንነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ምክትል ከንቲባው ለኢትዮጵያ ክብር መጠበቅም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።