አሸባሪው ንህወሓትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ በአርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ ከተሞች እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ንህወሓትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ በአርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ ከተሞች እየተካሄደ ነው
አርባ ምንጭና ሶዶ ጥቅምት 12/2015 (ኢዜአ) "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምፄን አሰማለሁ" በሚል መሪ ቃል አሸባሪው ህወሓትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ በደቡብ ክልል በአርባ ምንጭና በወላይታ ሶዶ ከተሞች እየተካሄደ ነው ።
የአርባምንጭ ከተማና አካባቢዋ ሕዝብ አሸባሪውን ህወሓት በማውገዝ ከማለዳው12 ሰዓት ጀምሮ ህዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
ሰልፈኞቹ የአንዳንድ የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም፣ የኢትዮጵያ ወዳጆችን የሚያመሰግኑና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍና አድናቆት የሚገልጹ መፈክሮችን እያሰሙ ይገኛሉ።
ሰልፈኞቹ “የትግራይ ክልል ህዝብ ወገናችን ነው፤ አሸባሪው ህወሓት ጠላታችን ነው፤ በድርድር ስም የህወሓትን ዕድሜ ማራዘም ይብቃ፤ በውክልና ጦርነት መጠቃት ይብቃ፤በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይቁም የሚሉ መፌክሮች እያሰሙ ነው።
በተመሳሳይ የወላይታ ሶዶ ከተማና አካባቢዋ ሕዝብ "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ! ድምፄን አሰማለሁ " በሚል መሪ ቃል ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄደ ነው።
ከወላይታ ዞን ሁሉም ወረዳዎች የተወጣጣ በሺህዎች የሚገመት ሕዝብ የተለያዩ መልክዕት የያዙ መፈክሮችን እያሰሙ ይገኛሉ።
ከመፈክሮቹ መካከል “ሀገራችንን ከዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በመታደግ ወደንና ፈቅደን በምንከፍለው መስዋዕትነት የግዛት አንድነታችንን እናስጠብቃለን፣ በሉዓላዊነታችን አንደራደርም፣ ህወሓት ቅጥረኛ ነው፤ በሰብዓዊ እርዳታ ስም የሚደረግ ጣልቃ ገቢነት ይቁም” የሚሉት ይጠቀሳሉ።
እንዲሁም የሀገርን ህልውና የሚፈታተን ማንኛውንም ዓይነት ጫናና ትንኮሳ እንደማይታገሱ የሚያስጠነቅቁ መዕልክቶችን እያስተላለፉ ነው።
ሰልፈኞቹ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሕልውና ለማስጠበቅና ለማስከበር ዋጋ እየከፈለ ለሚገኘው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ይገኛሉ።