ቀጥታ፡

አሸባሪውን ህወሃት የሚያወግዝና የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ህዝባዊ ሰልፍ በሰመራና ሎጊያ ከተሞች እየተካሄደ ነው

ጥቅምት 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) ”ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ አሸባሪውን ህወሃት የሚያወግዝ እና የምዕራባዊያንን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ በአፋር ክልል ሰመራና ሎጊያ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በሰልፋ ላይ የሰመራና ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በሰልፉም ምዕራባዉያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ያተገባ ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ አሸባሪዉ ህወሃት የታሪካዊ ጥላቶቻችን ተላላኪና ቅጥረኛ ነዉ፣ የሀገራችን ህልዉና ለማሰከበር ከመከላከያ ሰራዊታችንና መንግስት ጎን እንቆማልን የሚል መፈክር እየተሰማ ይገኛል።

እያካሄዱት ያለውም የተቃውሞ ድምፅ ለሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥበትና ለማስጠንቀቅም ጭምር እንደሆነ ነው ሰልፈኞቹ ድምፃቸውን ያስተጋቡት።

በተለይ አሸባሪው ህወሓትና ተባባሪ የውጭ ባንዳዎች የሚፈጥሩብንን የቡድን ጫናዎች በተባበረ ክንድና አንድነት ለማምከን ዝግጁ ነን ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ሰልፈኞቹ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አክብሮት፣ ድጋፍና አጋርነት በመግለጽ፤ ለሰራዊቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም