በቀቢፀ ተስፋ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው አሸባሪው ሕወሃት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲታደገው እየተማጸነ ነው- ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን - ኢዜአ አማርኛ
በቀቢፀ ተስፋ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው አሸባሪው ሕወሃት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲታደገው እየተማጸነ ነው- ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን
ጥቅምት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) በቀቢፀ ተስፋ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው አሸባሪው የሕወሃት ቡድን የዘረጋውን የዲፕሎማሲና የሚዲያ ትስስር በመጠቀም እንደልማዱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲታደገው ተማጽኖ እያሰማ መሆኑን የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን በቅርበት የሚከታተለው ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛ ተናገረ።
'ስኩፕ ኢንዲፔንደንት ኒውስ' የተሰኘው ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ኒውዝላንዳዊው ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ አሸባሪው ቡድን ሶስተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱ የተሳሳተ ስሌት ነበር ብሏል።
የሽብር ቡድኑ በሶስት እና አራት ሳምንታት ውስጥ ጦርነቱን በአሸናፊት ለማጠናቀቅ የነበረው እቅድ ፍጹም የሚሳካ እንዳልነበር ገልጾ፤ የቡድኑ አመራሮች ለጥፋት እቅዳቸው የትግራይን ህጻናትና ወጣቶች አስገድደው ወደ ጦርነት መማገዳቸውን ገልጿል።
የጦርነት መረጃ ኢ-ተገማች ቢሆንም እንኳን ቡድኑ ወደ ኋላ እያፈገፈገ ስለመሆኑና መንግስትም ሽሬ፣ አላማጣና ኮረም ከተሞችን ካለምንም ውጊያ መያዙን ይፋ ማድረጉን አውስቷል።
በዚህም ሕወሃት እንደተለመደው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሕልውናውን እንዲታደገው 'ኤርትራ ወረረችኝ' የሚል ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በማስተጋባት አንዳንድ የውጭ ኃይሎች እንዲታደጉት እየተማፀነ ነው ብሏል።
የሽብር ቡድኑ መሳሪያ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ከመቼውም ጊዜ በተጠናከረ አግባብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ መዝመታቸውን ጠቅሶ ዘመቻቸውም ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ገልጿል።
የአሸባሪው ሀወሃት ደጋፊዎችም በትግራይ ክልል 'የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል' በሚል መሰረተ ቢስ ውንጀላ በዲፕሎማሲው እና በመገናኛ ብዙሃን ረገድ ዓለም አቀፍ አጋር ለማሰበሰብ እየኳተኑ ስለመሆኑ ተናግሯል።
በግለሰብ ደረጃ ዊልያም ደቪሰን፣ አሌክስ ዴ ዋል፣ ማርቲን ፕላውት፣ ሸትል ትሮንቮል፣ ማሪያም ቫንደር ሪንግ የቡድኑ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል ናቸው ብለዋል።
የተወሰኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ሕብረትና የአሜሪካ ተቋማት መሪዎችም ዛሬም የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲባባስ እየቀሰቀሱ እና ለቡድኑ ድጋፍ እያሳዩ ስለመሆኑ ጠቅሷል።
በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አማካኝነት ተመድ አሁንም ዐይኑን ጨፍኖ ኢትዮጵያን እየኮነነ፣ አሸባሪውን ቡድን እያጀገነ መቀጠሉን ነው ጋዜጠኛው ያብራራው።
በተመሳሳይ የአውሮፓ ህብረት የተወሰኑ አመራሮች አሸባሪው ሀወሃት የቀሰቀሰውን ሶስተኛ ዙር ጦርነት እያወቁ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማድረጋቸው ከሽብር ቡድኑ አመራሮች ጋር ባላቸው ወዳጅነት የተነሳ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከአውሮፓዊያኑ 2018 ጀምሮ በሀገራዊ ለውጡ ዘርፈ ብዙ በጎ እርምጃ መውሰዱን ጋዜጠኛ ቶምሰን ገልጿል።
ጋዜጠኛው የሰሜኑ ግጭት ተቋጭቶ ነገሮች ወደ በጎ እንደሚመጡ፣ አሸባሪው ቡድንም በትግራይና በተቀረው ኢትዮጵያ የነበረው አገር የማተራመስ ተግባሩ እንደሚያከትም ተስፋ አለኝ ብሏል።