የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስጠበቅ መንግስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለሀገሩ የሚቆረቆር ሁሉ ሊደግፍ ይገባል-ፖለቲከኞች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስጠበቅ መንግስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለሀገሩ የሚቆረቆር ሁሉ ሊደግፍ ይገባል-ፖለቲከኞች
ጥቅምት 11/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስጠበቅ መንግስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለሀገሩ የሚቆረቆር ሁሉ ሊደግፈው እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገለጹ።
በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ፖለተከኞች መንግስት የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ እየሰራ ባለው ተግባር በተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ተናገረዋል።
ፖለቲከኛው አቶ የሽዋስ አሰፋ መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እየሰራ ካለው ተግባር ጎን ለጎን ታዋቂ ስዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉ የትግራይ አካባቢዎች ጉብኝት በማድረግ ህዝቡን ከጎናችሁ ነን ሊሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅታዊ ችግር የሚያልፍ በመሆኑ አንድነትን በማጠናከር አጋርነትን ማሳየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሌላኛው ፖለቲከኛ አቶ ሙሉ ብርሃን ኃይሉ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአንድነት በመነሳት ጊዜያዊ ችግሮችን በጋራ መቋቋምና የሽብር ቡድኑን ማስወገድ እንደሚገባው ተናግረዋል።
አቶ ሙሉ ብርሃን አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስና የስልጣን ጥሙን ለማርካት የትግራይን ህዝብ በተሳሳተ መረጃ በማወናበድ ወደ ጦርነት እየማገደ ነው ብለዋል።
በዚህ አፍራሽ ተልዕኮው የማይሳተፉ የትግራይ ተወላጆች ላይም ማስፈራሪያና ግድያ እየፈጸመ መሆኑን በመጥቀስ፤ይህ ተግባሩ ከምስረታው ጀምሮ ጥያቄ በሚያነሱ ታጋዮች ላይ ሲፈጽመው የኖረ ነው።
አሁንም በተለያየ ምክንያት በርካታ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጅምላ ግድያ በመፈፀም በሶስተኛ ወገን ለማሳበብና ኢትዮጵያን ለማዳከም ከሚጥሩ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም የሽብር ቡድኑ በትግራይ ህዝብና በመላው ኢትዮጵያ ያደረሰው ግፍና በደል በልኩ እንዳልተነገረ ጠቅሰው፤ የለኮሰውን ጦርነት ዳግም በማይቀሰቀስበት መልኩ መቋጨት ይገባል ብለዋል።
አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው መንግስት የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ የመከላከል እርምጃ ውስጥ እንዲገባ መገደዱን ነው የተናገሩት።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በሰላም እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ማሳየቱን ገልጸው፤ ይህም የሚደነቅ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ሰላም ለማስጠበቅ የሚወስዳቸው እርምጃዎችም ከመንግስት የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ ለሀገሩ ክብር ያገባኛል የሚል ሁሉ ሊደግፈው የሚገባ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ዋጋ ሲከፍል ኖሯል ያሉት አቶ ሙሉ ብርሃን፤ አሁንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን አሸባሪውን ህወሓት በቃህ ሊለው እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ይህን ማድረግ ከተቻለ በትግራይ ህዝብ ስም ሲነግዱ የኖሩ የሸብር ቡድኑ አመራሮች ለፍትሕ የሚቀርቡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።
አቶ የሽዋስ አሰፋ እንደተናገሩት ሀገር ከፖርቲና መንግስት በላይ በመሆኗ አንዳንድ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን በጋራ በመቆም መታገል ይገባል።
መላው ኢትዮጵያውያን ሀገር ለማስቀጠልና አንድነትን ለማስጠበቅ ከመንግስት ጎን በመሆን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።