ሚኒስቴሩ በደቡብ ክልል ለተፈናቃይ ወገኖችና ከስደት ተመላሾች የሚውል 320 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ በደቡብ ክልል ለተፈናቃይ ወገኖችና ከስደት ተመላሾች የሚውል 320 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥቅምት 11/2015 የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በደቡብ ክልል ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችና ለስደት ተመላሾች ድጋፍ የሚውል 320 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የገንዘብ ድጋፉን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ዛሬ ለደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው አስረክበዋል።
ሚኒስትሯ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት በለውጥ ጎዳና የተገኙ ድሎች በፈተና የታጠሩ ናቸው።
በእነዚህ ዓመታት ጦርነትን ጨምሮ ያጋጠሙ ሀገራዊ ፈተናዎች በተለይ በከተሞች ቀጥተኛ ተጽዕኖ ቢያሳርፉም ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም አካል በሆነው የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጪፕሮጀክት አማካኝነት በተለይ በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በቁጭት መልሶ መገንባት መቻሉን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
"ፈተናዎችም በትብብርና በአንድነት ከቆምን የተሻለ ሥራ መስራት እንደምንችል አረጋግጠውልናል" ብለዋል ሚኒስትሯ።
በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች በአማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ክልሎች ሚኒስቴሩ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፣ "ዛሬም በተመሳሳይ ለደቡብ ክልል 320 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል" ብለዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት ድጋፉ በሀገር ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች እና ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ለተመለሱ ወገኖች በቀጥታ የሚውል ሲሆን ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱም ያግዛል።
የፌደራል የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ መኮንን ያኢ በበኩላቸው እንዳሉት የፕሮጀክቱ አንዱ ዓላማ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው በከተሞች የተጠለሉተፈናቃይ ወገኖች የሚደርስባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና እንዲቋቋሙ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ነው።
"ለድንገተኛ ክስተቶች ምላሽ የሚሰጥ ፕሮጀክት አማካኝነት ከተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ለሀገር ውስጥ ተፈናቀዮች ድጋፍ ማድረግ ነው" ብለዋል።
በእዚህም በአማራ፣ አፋር እና ቤንሻንጉል ክልሎች ከ380 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች 900 ሚሊዮን ብር በመመደብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
የገንዘብ ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በክልሉ የጎርፍ አደጋ ባጋጠመ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፣ አሁን ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
በክልሉ በግጭትና እና በተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አቶ ርስቱ አስታውሰዋል።
"ለዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ 123 ሺህ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል አድርጓል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተፈናቀሉ 90 ሺህ ዜጎችን ደረጃ በደረጃ ወደቀያቸው በመመለስ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑንና የዛሬው ድጋፍም ለዚህ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።