ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጡ

ጥቅምት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውን ማብራሪያውን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

የመንግስት ልዑክ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ በታሰበው ውይይት ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠውላቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅና የግዛት አንድነቷን ለማረጋገጥ በምትወስደው እርምጃ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አይነት ጫና እንደማትቀበል መግለጻቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ ከሁሉም አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

በማብራሪያው ላይ የተሳተፉ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች መንግስት ለሰላም እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነትም ማድነቃቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም