ቀጥታ፡

በሉዓላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ኢ-ፍትሓዊ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም - የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት

ጥቅምት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሉዓላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ኢ-ፍትሓዊ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም ሲል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አስገነዘበ።

የጋራ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና በመቃወምና ነገና ከነገ በስቲያ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መርህ የሚካሄደውን ሰልፍ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም አንዳንድ የዉጪ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የያዙትን አቋም በጽኑ አውግዟል።

በተለይም የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ህብረት ከዚህ አቋማቸዉ እንዲታረሙ እና ለሰላም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ አሳስቧል።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተፈጠረዉን የሰላም ችግር በየትኛውም ቦታ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና በማንኛውም አጀንዳ ላይ በሰላማዊ መንገድ እና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለመነጋገር መንግስት አቋም መያዙን አስታውሶ፤ “የዉጪ ኃይሎች በተለይም የተባበሩት መንግሰታትና የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የያዙት አቋም የሀገሪቱን ንጹሐን ዜጎች የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ ኢ-ፍትሓዊ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም” ብሏል፡፡

ስለሆነም እነዚህ የውጭ ሃይሎች ከዚህ አቋማቸዉ እንዲታረሙ እና ለሰላም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል።

በአፍሪካ ህብረት የተጀመረዉን የሰላም ዉይይትና ድርድር ጥረት ከግቡ ለማድረስ እንዲቻል ምዕራባዊያን የሀገሪቱን የሉአላዊነት ክብር ሳይጥሱ፣ በሎጂስቲክስ እና አግባብነት ባለው ሙያዊ ድጋፍ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ የጋራ ም/ቤቱ በአጽንዖት ጠይቋል።

ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በመላ አገሪቱ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የሰልፍ መርሀ-ግብር ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም የሀገራችንን ሉዓላዊነት ያላከበረና ሕዝባችንን ህልውና ያላገናዘበ የዉጪ ጫና እንዲቆም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምጽ እንድናሰማና በጋራ እንድናወግዝ ሲል የጋራ ም/ቤቱ ጥሪዉን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም