የቡና ምርት አሰባሰብ በጥንቃቄ ሊሰራ ይገባል-የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን

ጥቅምት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) ወቅቱ የቡና መሰብሰቢያ በመሆኑ የሚፈጠረውን የምርት ጥራት ጉድለት ለማስቀረት አምራቾች በጥንቃቄ እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጥሪ አቅርቧል።

የቡና አምራች ክልሎች ብሔራዊ የቡና ምርት የጥራት ንቅናቄ መርሐ ግብር ሊካሔድ ስለመሆኑ ባለስልጣኑ አስታውቋል።

መርሐ ግብሩ ከጥቅምት 15 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።

የባለስልጣኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሸምሱ የጥራት ንቅናቄ መርሐ ግብሩ ''የቡና ምርት ጥራት ለዘላቂ ዕድገት'' በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሔድ ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩ በተለያዩ ቀናት በሚዛን፣ ጅማ እና ሐዋሳ እንደሚካሔድ ጠቁመው፤ አምራቾች፣ ማህበራት፣ ዩኒዬኖች፣ ላኪዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ተመራማሪዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

በመርሐ ግብሩም ላይ የእሸት ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች፣ የቡና ዘር ዝግጅት፣ የችግኝ ጣቢያዎችና ሌሎች የዘርፉ አጋዦች እንደሚጎበኙ ጠቅሰዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የቡና ጥራትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ሰነዶች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን፤ የመስክ ጉብኝት እንደሚኖርም ገልጸዋል።

ሁነቱ የቡና ምርትን መሰብሰብ በተጀመረበት ጊዜ የተገጣጠመ በመሆኑ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ወደ ሥራ ለመግባት እንደሚያስችል ነው ያብራሩት፡፡

በባለስልጣኑ የምርት ዝግጅትና አግሮ ፕሮሰሲንግ ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ሞላ ደምሴ በበኩላቸው፤ "የቡና ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ክትትልና እንክብካቤ ማድረግ" አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም "በምርት አሰባሰብ፣ አዘገጃጀትና አያያዝ ወቅት ከፍተኛ የጥራት መጓደል እንደሚያጋጥም ጠቅሰው፤ በዚህ ወቅት አምራቾች  ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ" እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተያዘው የምርት ዘመን የታጠበና ያልታጠበ ቡና በጥራት ለማዘጋጀት 2 ሺህ 843 ኢንዱስትሪዎች ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መግባታቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም