ዳያስፖራው ኢትዮጵያን በሚጠቅም አጀንዳ ላይ በማተኮር መስራት ይኖርበታል - ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ኢትዮጵያን በሚጠቅም አጀንዳ ላይ በማተኮር መስራት ይኖርበታል - ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ
ጥቅምት 11 2015(ኢዜአ) ዳያስፖራው ኢትዮጵያን በሚጠቅም አጀንዳ ላይ ብቻ በማተኮር አንዳንድ የውጭ ሃይሎች በአገሪቷ ላይ እያደረጉት ያለውን ጫና በጋራ መከላከል እንደሚገባው 'ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ' የተሰኘው ጥምረት አስታወቀ።
የጥምረቱ የዩናይትድ ኪንግደምና የቤልጂየም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዘላለም ጌታሁን እና አቶ ኤፍሬም ዘውዱ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች አሸባሪው ሕወሃት የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ መንግስት እያደረገ ያለውን የመከላከል እርምጃ በማዛባት መሰረተ ቢስ ክስ እያስተጋቡ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በአውሮፓ አገራት የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ የኢትዮጵያን እውነታና የሽብር ቡድኑን ግፍ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወቀው እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ጥምረቱ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረር አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ባለስልጣናትን ማናገርና ሰላማዊ ሰልፎችን በማካሄድ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በሕዝብ ፍላጎት የመጣውን ለውጥ ከማደናቀፍና በታሪክ ተጠያቂ ከሚያደርጋቸው ተግባራት መቆጠብ እንዳለባቸው የሚያሳስቡ መልዕክቶች በተለያዩ አማራጮች እያስተላለፉ እንደሚገኝ ነው አስተባባሪዎቹ የገለጹት።
እየተከናወኑ ባሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች የአውሮፓ አገራት በተወሰነ መልኩ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ያላቸው አረዳድ መሻሻል እየታየበት ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑን አገር የማፍረስ ተልዕኮ የሚደግፉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን በጋራ የመመከት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ዳያስፖራውም የአሸባሪው ሕወሃትን ከፋፋይ አጀንዳ ወደ ጎን በማለት አገርን በሚጠቅም አጀንዳ ላይ በመስራት አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና ጫና የሚቃወም ሰልፍ ትናንት በቤልጂየም ብራሰልስ የአውሮፓ ኮሚሽን ፊት ለፊት መካሄዱ ይታወቃል።