ቀጥታ፡

ፈተናው ለትምህርት ጥራትና ለእርስ በርስ ግንኙነት መጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው-የ12ኛ ክፍል ፈታኝ መምህራን

ደሴ ጥቅምት11 ቀን /2015 (ኢዜአ) "የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ካለው ፋይዳ ባሻገር የእርስ በርስ ግንኙነት ያጠናክራል'' ሲሉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ፈታኝ መምህራን ተናገሩ።

ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፈታኝ መምህር አብዱረህማን ጅሎ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ኩራጅን አስቀርቷል።

"ይህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተሰጠው ፈተና በተረጋጋ ሁኔታ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ከፈተና ሂደቱ ብዙ ትምህርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

"በፈተናው ከተለያዩ አካባቢዎች የመጣን መምህራን በጋራ መገናኘታችን ከባህልና እሴት ልውውጥ ባለፈ የተፈጥሮ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን ለማወቅና ለመጎብኘት አስችሎናል" ብለዋል።

"ፈተናው የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር አንድነታችንን ለማጎልበት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል" ሲሉም ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የወሎን ህዝብ የአብሮነት፣ የፍቅርና የመቻቻል ባህል ማየታቸውን ጠቁመው፤ ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ ያዩትን ባህል ለማስተዋወቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የመጡበትን አካባቢ ባህልና እሴት ማስተዋወቃቸውን የገለጹት መምህር አብዱረህማን፤ "አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን የኢትዮጵያን ከፍታ በጋራ ማረጋገጥ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

በፈተና ቁጥጥር ሥራ የተመደቡት አቶ ተመስገን ወጋሪ በበኩላቸው፣ ፈተናው በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።

"ዘንድሮ ፈተናው በተለየ ሁኔታ መሰጠቱ ተማሪዎች ቀድመው እንዲዘጋጁ ያደርጋል፤ በኩረጃ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የሚያቋርጡ ተማሪዎችንም ቁጥር ይቀንሳል" ብለዋል።

"የወሎ ህዝብ የአብሮነት ባህልና እንግዳ ተቀባይነት መቼም ከውስጤ አይጠፋም" ያሉት አቶ ተመስገን፣ በቆይታቸው የመጡበትን አካባቢ ባህልና እሴት ማስተዋወቃቸውን ተናግረዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አወል ሰይድ በበኩላቸው ሁለተኛው ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላማዊ መንገድ መሰጠቱን ገልጸዋል።

"ከፈተናው ጎን ለጎን ፈታኝ መምህራን፣ ፈተና ተቆጣጣሪዎችና ተፈታኝ ተማሪዎች የወሎን የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቦታዎችን በማስጎብኘት አንድነታቸውን እንዲያጎለብቱ ተደርጓል" ብለዋል።

"ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ትውልዱ ፈተናን በራሱ ብቻ እንዲሰራ ያደርጋል" ብለዋል።

ፈተናውን በራሳቸው የሰሩ ተማሪዎች የልፋታቸውን ውጤት እንዲያገኙ ከማድረጉ ባለፈ በአቋራጭ የማለፍ ባህልን ለመጠየፍ ጠቃሚ መሆኑን ዶክተር አወል ገልጸዋል።

መንግስት ዘንድሮ በ12ኛ ክፍል ፈተና ያሳየውን ጥንካሬ በቀጣይ በየደረጃው ባሉ የትምህርት እርከኖች እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛው ዙር ከ14 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የተሰጠው ፈተና ዛሬ በሰላም ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም