ወጣቱ የለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆን በተረጋጋና አስተውሎ በተሞላበት መንገድ ሊንቀሳቀስ ይገባል...አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

68
ወልዲያ  መስከርም 13/2011 ወጣቱ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ ባመጣው አዲስ ለውጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለውጡን በተረጋጋና አስተውሎ በተሞላበት መንገድ ማስቀጠል እንዳለበት የግንቦት 7 ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተናገሩ። የግንቦት 7 አመራሮች ከወልድያ ከተማ ሕዝብ ጋር ዛሬ ውይይት አካሂደዋል። ወጣቱ በነበረው የአገዛዝ ስርዓት ክፉኛ በመማረሩና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ባለመሆኑ ጠንካራ ትግል በማድረጉ አሁን የተገኘው አገራዊ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሥራ እጥነት ችግር፣ የዴሞክራሲ እጦትና መሰል ውስብስብ ችግሮች ህዝቡ አደባባይ ገንፍሎ እንዲወጣ ያነሳሳው መሆኑን ገልፀዋል። በተለይም የወልድያና የአካባቢው ወጣቶች ለውጡ ይመጣ ዘንድ የማይተካ ህይወታቸውን ከመገበር ባለፈ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውንና የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው አቶ አንዳርጋቸው አስታውሰዋል። በተከፈለው መስዋዕትነት ባለፉት ጥቂት ወራት ተስፋ ሰጪና አዲስ የለውጥ ብርሃን በሀገሪቱ መፈንጠቁን ገልጸው "የተጀመረው ለውጥ ዳር እንዲደርስ፣ ወጣቶች ያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲፈቱና ለውጡ በጠንካራ መሰረት እንዲቆም የበኩላቸውን ማገዝ አለባቸው" ብለዋል። መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት አገሪቱ ተጋርጦባት ከነበረው አደጋ ለመታደግ ባደረገውን ጥሪ መሰረት ግንቦት 7 ወደ ሃገር ቤት በመምጣት የዳበረ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እየሰራ መሆኑንም አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል። በወልድያ ባህል አዳራሽ የከተማው ሕዝብ ተገኝቶ በተደረገው ውይይት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም አቶ አንዳርጋቸው ምላሽ ሰጥተዋል። በእዚህም "በተለያየ ምክንያት አሸባሪ ተብለው የታሰሩና እስካሁን ድረስ ያልተፈቱ ወገኖች እንዲፈቱ ለማድረግ ድርጅታቸው ግንቦት 7 ከመንግስት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲያገኙ ይሰራል" ብለዋል። ለነፃነት ሲታገሉ ለተገደሉት ወገኖችም ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ "የራያና ወልቃይት መሬት ጉዳይም በህግ መታየትና ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ድርጅታችን ያምናል" ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፣  ለእዚህም ግንቦት 7 ትኩረት ሰጥቶ እንደሚታገል አረጋግጠዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም