ቀጥታ፡

አንዳንድ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና የሚያወግዙ ሰልፎች በተለያዩ ክልል ከተሞች ሊካሄድ ነው

ጋምቤላ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ሰቆጣ እና ወልዲያ (ኢዜአ) ጥቅምት 11/2015 በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ያልተገባ ጫና ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ያሉ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ህወሓትን የሚያወግዙ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች ነገና ከነገ በስትያ በተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የጋምቤላ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ ላይ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ያልተገባ ጫናና ጣልቃገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ ነገ በጋምቤላ ክልል ይካሄዳል

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዴንግ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሰልፉ የሚካሄደው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ አንዳንድ ምዕራባውያን እያደረጉ ያለውን ጫና በመቃወም ነው።

ስለሆነም የክልሉ ህዝብ ነገ ጥቅምት 12 ቀን 2015 የተቃውሞ ሰልፋ ያካሂዳል ብለዋል።

በሰልፉ ላይ ህዝቡ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ ጫና ከማውገዝ ባለፈ የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ሴራ የዓለም ማህበረሰብ እንዲረዳ ድምጹን በአንድነት ያሰማል ብለዋል።

በተጨማሪም የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በግንባር ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን ህዝባዊ ደጀንነትም የሚገለጽበት ሰልፍ መሆኑን አቶ ኡገቱ ተናግረዋል።

ሰልፉ በጋምቤላ ከተማ፣ በክልሉ ሦስት የዞን ከተሞችና በሁሉም የወረዳ ከተሞች እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በደብረብርሃን እና ደሴ ከተሞች እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የሰሜን ሸዋ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ እንንደተናገሩት፣ የዞኑ ህዝብ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

አሁንም ኢትዮጵያ ያላትን እውነታ ለማሳየትና አንዳንድ የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ያልተገባ ጫና ለማውገዝ ሰልፍ ያካሂዳል።

ህዝባዊ ሰልፉ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ሕዝብን ለማሰቃየት አልሞ ሕፃናትን ጭምር በጦርነት እያሰለፈ ያለውን ህወሓት የሚደግፉ አንዳንድ የውጭ ሃይሎችን የሚቃወም ነው።

በሀገርና በህዝብ ላይ የተለያዩ ወንጀሎች እየፈፀመ ያለን ቡድን ለመደገፍ ሲባል በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ጣልቃገብነት ይብቃ የሚሉ ምልክቶችም ይተላለፋሉ ብለዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳዳር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ብዙነህ በበኩላቸው፤ እንዳሉት፣ አንዳንድ ምዕራባዊያን የአሸባሪውን ህወሓት ህልውና ለመታደግ ሲሉ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚዳፈር ጣልቃ ገብነት እያሳዩ ነው።

በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ የሀገርና የግለሰብ ሀብት ከማጥፋት ባለፈ በርካታ ንጹሀን ዜጎች ለሞትና ለመፈናቀል መዳረጋቸውን ወይዘሮ መቅደስ አስታውሰዋል።

"ለእዚህ የጥፋት ቡድን ውግንናቸውን እያሳዩ ያሉ አንዳንድ የውጭ ሀይሎች የኢትዮጵያን ሉአላዊነት መዳፈርና ጣልቃ ገብነታቸውን ለመቃወም በመጪው እሁድ ሰላማዊ ሰልፉ ይካሄዳል" ብለዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት፤ በሰልፉ ላይ ከ85 ሺህ በላይ ሕዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።

"የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቀወምና የመንግስትን ሀገር የማዳን ተግባር የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በመጪው እሁድ በደሴ ከተማ ይካሄዳል'' ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም ሙስጦፋ ናቸው።

በሰልፉ ላይ "በእጅ አዙር ቅኝ አንገዛም! ፣ አሸባሪው ህወሓት አገር አፍራሽ ነው! ፣ መንግስት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚወስደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ እንደግፋለን!" የሚሉና መሰል መልዕክቶች እንደሚተላለፉ ገልጸዋል።

"ህዝቡም ለዓለም ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ በማሳወቅና ያልተገባ ጫናን በመቀዋወም ድምጹን በአንድ ላይ ያሰማል" ሲሉ ልፀዋል።

አቶ አብዱልከሪም እንዳሉት በሰልፉ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሃይማት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ ህዝባዊ ሰልፉን በሰቆጣ እና በወልዲያ ከተሞች ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቃል።

የሰቆጣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መላሽ ወርቃለማው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሰልፉ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ!” በሚል መሪ ቃል በመጪው እሁድ ይካሄዳል።

ህዝባዊ ሰልፉ አንዳንድ ምእራባውያን ና ተቋሞቻቸው የሽብር ቡድኑን በመደገፍ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለመዳፈር እያደረጉት ያለወን ተፅእኖ የሚቃወም መሆኑን ተናግረዋል።

"በእለቱም ኢትዮጵያን የወደደ ለኢትዮጵያ ይቆማል! ፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን በጋራ ቆመን እንከላከላለን! ፣ በውጭ ሃይሎች የሚፈፀምብንን ጫና አጥብቀን እንቃወማለን! የሚሉና መሰል  መልዕክቶች ይንጸባረቃሉ" ብለዋል ።

"በወልዲያ ከተማ አንዳንድ የውጭ ሀይሎች በሰብአዊነት ስም በአገራችን ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ህዝባዊ ሰልፍ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል" ያሉት ደግሞ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ዳዊት ታደሰ ናቸው።

በሀገር ህልውና ላይ እየመጣ ያለውን የአንዳንድ ምእራባውያን ሴራ ለመቃወም የከተማው ህዝብ  በመጪው እሁድ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን እንደሚያሰማ ተናግረዋል።

በተጨማሪ ህዝባዊ ሰልፉ በህይወት መስዋዕትነት ጭምር ሀገርን እያጸና ላለው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፉን የሚያጠናክርበት መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ ቅደመ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም