ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ እና አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያደርገው ጥረት ሊደግፍ ይገባል--ኤፓክ

ጥቅምት 11/2015 (ኢዜአ) አሜሪካን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰበዓዊ እርዳታን ለማቅረብ እና አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያደርገውን ጥረት ሊደግፍ ይገባል ሲል አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ (ኤፓክ) ገለጸ።

የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መስፍን ተገኑ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ የሰላም ሂደቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን በጎ ተግበራት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች የጀመረውን ጦርነት በመከላከል በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞችን ከሽብር ቡደኑ ነጻ በወጡ የክልሉ አከባቢዎች ሰበአዊ እርዳታን ለማቅረብ እያደረገ የሚገኘው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ቡድኑ በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንዳይመጣ ፤ የሰበአዊ እርዳታ ተደራሽ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው መንግሥት የህዝቡን ሰላም የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ መስፍን የሰበአዊ እርዳታን ለማቅረብ የፈረሱትን የመሰረተ ልማት መልሶ መገንባት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነት ሊደግፍ የሚገባው በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም