የአሸባሪው ህወሓት ሕልውና መክሰም ሞት የሆነባቸው አንጋሾች

78

በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ የዘመናዊ ቅኝ ገዢዎች ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነው አሸባሪው ህወሓት ሕልውና መክሰምና መክሰሙንም መቀበል ለአንጋሾቹ ሞት ሆኖባቸዋል።

በተፈጥሮ ሃብት፣ በመልካም አየር ጸባይና በሰፊ የሰው ሃይል ከሚታወቁት የአፍሪካ አገራት አንስቶ በፓስፊክ፣ ላቲንና ኤዢያ እንዲሁም ዓረብ ሀገራት የምዕራባውያን እጅ ከመርዘምም ያለፈ አንጋሽና አውራጅ ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል።

በሀገራቱ የአንዳንድ ምዕራባውያንን ጉዳይ የሚያስፈጽም፣ በነሱ ዳረጎት የሚኖር፣ የሚሉትን የሚያደርግና ዜጎቹን አፍኖ ያለ ለውጥ ለመኖር ቃል የገባውን ያነግሱታል፤ በተቀራኒ ቆሞ ለሕዝቡ ተጠቃሚነትና ለሀገሩ ሉዓላዊነት የሚሰራውን ደግሞ በተወሳሰበ ሴራና በሚዲያቸው ሐሰተኛና የፈጠራ ስራ ያስወግዱታል ስሙን በማጠልሸት የተሳሰተ ግንዛቤ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

ለዚህም ከአፍሪካ ሊቢያን፣ ከአረብ ሀገራት ኢራቅና ሶርያን ከአውሮፓ ቤላሩስ፣ እንዲሁም ሌሎች ሀገራትን መጥቀስ ይቻላል።

ሀገራችን የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናም የአለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቁልፍ ስፍራ በመሆኑ የምዕራባውያኑን አይን፣ ልብና ቀልብ ከሳበ ዘመናት ተቆጥረዋል።

ምዕራባውያኑ በዚህ ቀጠና ጉዳይ አስፈጻሚና የሕልውናቸው አስቀጣይን ለመሾም ለዓመታት ያደረጉትን እንቅስቃሴ የአገራችን ጠንካራ መንግሥታት በጦርም በፖለቲካም ሲመክቱት ሲያሸንፉት መቆየታቸው ታሪክ ምስክር ነው።

ይህ ሀገር ወዳድነትና በራስ ለራስ የመቆም ሐላፊነት ግን አሻባሪው ሕወሃት በአንጋሾቹ ምዕራባውያን ድጋፍ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ እንዲጠፋ ሆኖ ተሰረቷል።

አሸባሪው የምዕራባውያን ጉዳይ አስፈጻሚ ከመሆን ያለፈ ሀገር የማጥፋት ሚና ሲወጣ ቆይቷል፤ ይህንንም ትውልድ በሚታነጽበት የትምህርት መስክ፣ የሀገር የመጨረሻው መከታ በሆነው መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵየን አንጡራ ሀብት በማሸሽ፣ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማንጎተት፣ በመዝረፍና ሙስናን በማስፋፋት ላለፉት ከ27 በላይ አመታት ሲተገብር ቆይቷል።

ይህም ምዕራባውያን በቀጠናው የሚፈልጉት መንግስት ባህርይ ስለሆነ እንደ በኩር ልጅ እንዲንከባከቡት ከማድረግ ባለፈ የህልውናው ጠባቂ እስከመሆን እንዳደረሳቸው የለውጡ መንግስት ከመጣ ወዲህ ኢትዮጵያ የአለም አጀንዳ እንድትሆን ያደረጓት ክስተቶች ምስክር ናቸው።

አሸባሪው የህዝቦች ትግል ካመጣው ለውጥ ተቀራኒ በመሆን የትግራይ ክልል ህዝብን መደበቂያ በማድረግ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ፈጽሞ በሀገር ላይ ሶስት ጊዜ ጦርነት አውጇል።

አሸባሪው የቀረበለትን የሰላም አማራጭ በመተው በህዝብ ላይ የፈጸማቸውን ወረራዎች ለመከላከልና ሀገርን ከመበተን ለመታደግ መንግስት ወደ እርምጃ ሲገባ የአንጋሾቹ ምዕራባውያን ጨኸት የጀምራል።

ይልቁንም ወደ ጎረቤት ክልሎች ያደረገውን ወረራ በመመከት አሸባሪውን የመከላከል እርምጃ ሲወሰድ የሽብር ቡድኑም መዳከሙ ሲታወቅ አንጋሾቹ ምዕራባውያን ጩኸታቸው በተመሳሳይ ጊዜ በተለያየ ቦታ እኩል ይሰማል።

የሚጋልቡት ፈረስ የደከመና ወደ ሞት የደረሰ ሲመስላቸው ቆመንለታል የሚሉትን የሉዓላዊነት መከበር፣ የዴሞክራሲና ሰብዓዊነት መብት መስፈን ጥሰው የዛቻ ጦርነትና የሀሰተኛ ትርክት ጩኸተቸውን ያሰማሉ።

ይህም ሰሞኑን አሸባሪው በከፈተው ሶስተኛ ዙር ጦርነት ተመክቶ መፈራረስ ሲጀምር ጭምብላቸው ወልቆ እንዲታዩ አድርጓል፤ ከአለም ተቋማት መሪዎች ገለልተኛ እስከሚባሉ ሚዲያዎች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች እስከ ቅልብ ጉዳይ አስፈጻሚ (ሎቢስቶች) ድረስ ተመሳሳይ አለም አቀፍ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ ተነስቷል።

መንግስት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል የሰላም አማራጭ ሲያመጣም የአፍሪካ ህብረትን አናምንም ሌላ አካል ይዳኘን በሚል አሸባሪው ሲደነፋ ዘምም ያሉት ምዕራባያውን ህልውናው እየከሰመ መሆኑን ሲያውቁ ድርድር ይቅደም ጦርነት ይብቃ የሚል ዜማ ከማቀንቀን አልፈው ለወራት ያዘጋጁትን ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጩ ነው።

በአሸባሪው ሕወሃት እንግልት እየተሰቃየ የሚገኘውን የትግራይ ክልል ህዝብን እንደ መጠቀሚያ በማድረግ ክሳቸውን ቢያሰፉም የህዝብ ልጅ የሆነው መከላከያ ሠራዊት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ግን የሚገኘው ሕዝብ ምስክርነት ጩኸታቸውን አጋልጦ የእውነተ ምስክር ሆኗል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕይወቱን በመስጠት የሚያጸናውን የሀገር ሕልውና ሁሉም በተሰማራበት መስክ በመረጃ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ ግንዛቤ በመፍጠር ሊያግዝና አሸባሪውን እንዲሁም አንጋሾቹን ሊከላከላቸው ሊመክታቸው ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም