ግብርን በሀቀኝነት በመክፈል የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆንን በተግባር ማሳየት ይገባል--ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

129

ጥቅምት 11/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ፈተና ላይ ባለችበት ወቅት ግብርን በሀቀኝነት በመክፈል የሀገር የቁርጥ ቀን ልጅ መሆንን በተግባር ማሳየት እንደሚገባ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

የግብር ግዴታቸውን በወቅቱና በትክክልኛው መንገድ ለሚወጡ ኢትዮጵያውን መንግስት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ለአራተኛ ጊዜ ባካሄደው የፌደራል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች 400 ለሚሆኑ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች የዕውቅናና የሽልማት መርኃ-ግብር አካሂዷል።

“እናመሰግናለን፤ግብር ለሀገሬ” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የእውቅና መርኃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።

ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ ድርጅቶችና ግለሰቦችም የፕላቲኒየም፣ የወርቅ እና የብር ደረጃ ሽልማታቸውን ከኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ ተቀብለዋል።

ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ግብርን በወቅቱና በትክክለኛው መንገድ መክፈል ከማንኛውም የሚሰራና የሚያመርት ዜጋ የሚጠበቅ ግዴታ ነው።

ግብርን በመክፈል ግዴታውን የተወጣ ዜጋም እንደ መንገድ፣ ትምህርት ቤት እና መሰል መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡለት መንግስት የመጠየቅ መብት እንዳለው ገልጸዋል።

“የምናከብራችሁ በአንጻሩ ግብር የማይከፍሉ በመኖራቸው ነው፤የምንሸልማችሁም አገር ስትለማና ስታድግ እኔም ከውጤቱ የበለጠ ተጠቃሚ ነኝ ከሚል የዜግነት ግዴታ የሚርቁ በመኖራቸው ነው” ብለዋል።

"ሀገር በተፈተነችበት ወቅት ወገኔ ይማር፣ ጤናው ይጠበቅ፣ መንገድ ይሰራለት፣ ውሃ ይግባለት" በሚል ግዴታቸውን በመወጣታቸው እውቅናው ጎለቶ እንዲታይ ስለማድረጉ ጠቁመዋል።

“ሀገራችን በተፈተነችበት ጊዜ በአቋራጭ ለመክበር የሚጥር፣ በሕገወጥ መንገድ ሀብት የሚያሸሽ፣ ንብረቱን የማያስመዘግብ፣ የእናት ቤት ሲጎዳ ለመዝረፍ የሚሮጥ መኖሩን ደግሞ መዘንጋት የለብንም” ብለዋል።

በመሆኑም ግብርን በሀቀኝነት በመክፈል የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆንን በተግባር ማሳየት እንደሚገባ በመጥቀስ።

መንግስትና ግብር ከፋዩ በመተባበር ከኢኮኖሚው ተመጣጣኝ ገቢ በመሰብሰብ ለአገር ልማት እንዲውል ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በወቅቱና በትክክለኛው መንገድ የግብር ግዴታቸውን ለሚወጡ ኢትዮጵያውን መንግስት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን አረጋግጠዋል።

የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዐይናለም ንጉሴ በገቢና በህግ ተገዥነት የተመዘኑ 400 ታማኝ ግብር ከፋዮችን ሚኒስቴሩ በፕላቲኒየም፣ በወርቅና በብር ደረጃ እውቅና እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

ግብርን በታማኝነት የሚከፍሉ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ግብርን የሚሰውሩና የሚያጭበረብሩ እንዳሉ ተናግረዋል።

የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር በመዘርጋት የግብር ስወራና ከማጭበርበር ድርጊትን ለመከላከል ከ17 ባንኮች ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩም በ2014 በጀት ዓመት 336 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 95 በመቶ ማሳካት እንደተቻለና በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመትም 450 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም