ነገ በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች

163

ጥቅምት 11/2015 /ኢዜአ/ ነገ በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል አስታወቀ።

የድጋፍ ሰልፉ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

"ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምፄን አሰማለሁ" በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች ጥቅምት 12 እና 13 የድጋፍ ሰልፍ እንደሚካሄድ ይታወቃል።

ህዝባዊ ሰልፉ መንግስት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት ለማስከበር የሚያደርገውን የመከላከል እርምጃ የሚደግፍ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሲሆን ይኸው የድጋፍ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ/ም እንደሚካሄድ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል አስታውቋል።

ፕሮግራሙ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱንም የጋራ ግብረ ሀይሉ ጨምሮ ገልጿል።

በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት:-• ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከኤድናሞል በአትላሳ ወደ ካዛንቺስ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል አደባባይ ላይ

• ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ አራተኛ ክፍለጦር• ከጎፋ በአዲሱ መንገድ ወደ ለገሃር ለሚመጡ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን መስቀለኛ ላይ

• ከቡልጋሪያ በሜክሲኮ አደባባይ ወደ ለገሃር የሚሄዱ ለገሀር

• ከሳር ቤት ወደ ሜክሲኮ አደባባይ እንዲሁም ከጦር ኃይሎች በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደ ለገሃር የሚወስደው ሜክሲኮ አደባባይ

• ከተክለ ሃይማኖት በጎማ ቁጠባ ወደ ለገሃር ሰንጋተራ 40/60 ኮንደሚንየም አካባቢ

• ከጌጃ ሰፈር ፣ በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች ጎማ ቁጠባ አካባቢ

• ከመርካቶ በተክለ ሃይማኖት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሜትሮሎጂ በር ላይ

• ከራስ ቴአትር በጎላ ሚካኤል ውስጥ ለውስጥ ጎላ ሚካኤል መስቀለኛ መንገድ ላይ

• ከተክለ ሃይማኖት ጥቁር አንበሳ ኢሚግሬሽን ጥቁር አንበሳ ሼል አጠገብ• ከፒያሳ በቸርችል ጎዳና ለገሃር ቴዎድሮስ አደባባይ

• በአሮጌው ቄራ ፍል ውሃ ንግድ ማተሚያ ቤት አካባቢ

• ከካዛቺስ ወደ ሂልተን ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ

• ከአዋሬ በካዛንቺስ ወደ ፍል ውሃ የሚወስደው መንገድ ፍል ውሃ አካባቢከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪዎች ዝግ እንሚደረግ አሽከርካሪዎች አውቀው አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ እና በተገለፁት መንገዶች ላይ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ እንዲሁም ከአርብ ምሽት ጀምሮ ተሽከርካሪ ማሳደር ፍፁም ክልክል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

በመጨረሻም ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት 991 ወይም 816 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 01- 11 -11- 01 -11፣ 01- 11- 26- 43- 59 እንዲሁም በ01- 11- 01- 02- 97፣ መጠቀም የሚችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም