በሩብ ዓመቱ 314 ሚሊዬን ብር ገቢ መሰብሰቡን የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ገለጸ

ጭሮ ጥቅምት 11/2015 በሩብ ዓመቱ 314 ሚሊዬን ብር ገቢ መሰብሰቡን የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ገለጸ።

ዞኑ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ለመሰብሰብ ካቀደው 376 ሚሊዬን ብር 314 ሚሊዬ በር መሰብሰብ መቻሉን ገልጿል።

የዞኑ ገቢዎች ባለሰልጣን ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሀሰን አብደላ፤ ዕቅዱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ56 ሚሊዬን ብር ብልጫ አለው ብለዋል።

በቀጣይም በዞኑ የ'ቦርዶዴ' ኬላ ስራ በመጀመሩ የበለጠ ገቢ ለመሰብሰብ አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የግብር አሰባሰቡም ከሙስናና ብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በዚህም ማንኛውም የገቢዎች ሰራተኛ ከገንዘብ ጋር የማይነካካበት ዘዴ በመዘርጋቱ ሴክተሩ ከሙስና ስጋት ነፃ ሆኗል ብለዋል፡፡

የጭሮ ከተማ  ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት የታክስ ኦዲት ቡድን መሪ አቶ አደመ ብርሸት በበኩላቸው በከተማዋ በሩብ ዓመቱ 45 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 37 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡

በከተማዋ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር ማስገባት መቻሉ ለተሰበሰበው ገቢ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

ሕዝቡም ግብር መክፈል አገር ወዳድነትና የዜግነት ግዴታ መሆኑን እንዲረዳ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል።

በጭሮ ከተማ ግብር ሲከፍሉ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፈለቀች አበበ፤ ግብር መክፈል ግዴታቸው መሆኑን አውቀው ግብርን በጊዜው እየከፈሉ መሆኑን ይናገራሉ።

ሆኖም አሁንም ግብር ከፋዩ ሳይጉላላ ግዴታውን እንዲወጣ ቀልጣፋ አሰራር አለመኖሩን አንስተዋል።

በመሆኑም የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው ይህ ሲሆን ብዙ ሰው ግዴታውን ይወጣል ብለዋል።

ሌላው ግብር ከፋይ አቶ አህመዲን መሀመድ ''ግብር በመክፈል ህጋዊ መሆኔን አረጋግጬ ከመንግስትም ከህግም ሳልደብቅ ቀና ብዬ እድንቀሳቀስ ረድቶኛል'' ብለዋል፡፡

ግብር "ከሕዝብ ወደ ሕዝብ" በመሆኑ ሁሉም ግብርን በመክፈል የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት መተባበር ይኖርበታል ሲሉ መልዕታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም