ቀጥታ፡

በአሸባሪው ህወሃት ዘረፋና ውድመት ተቋርጦ የቆየው የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታን መልሶ ለመጀመር እየተሰራ ነው

ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ)  በአሸባሪው ህወሓት በተፈጸመበት ዘረፋና ውድመት ግንባታው ተቋርጦ የቆየው የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታን መልሶ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።

በኮርፖሬሽኑ የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር በኃይሉ ስንታየሁ በሰጡት መግለጫ፤ 390 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ ልማት ፕሮጀክት በሽብር ቡድኑ በተፈፀመ ጥቃትና ዝርፊያ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል።

በዚህም ትላልቅ ማሽኖችንና የኤሌክትሪክ ኃይል ሲስተሞችን ጨምሮ በርካታ ልዩ ልዩ የፕሮጀክቱ ንብረቶች በቡድኑ ዘረፋና ውድመት እንደተፈጸመባቸው ገልፀዋል።

የደረሰውን ጥፋት በአግባቡ ለመለየትና የጥፋቱን መጠን ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አሸባሪው ህወሓት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በየቦታው የበተናቸውን ንብረቶች የመሰብሰብ ሥራ መከናወኑንም አመልክተዋል።

አጠቃላይ የፕሮጀክቱን ግንባታ መልሶ ለመጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተቋራጭ ኩባንያው ጋር ንግግር ተጀምሯል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኮምቦልቻ የሚገኘውን የፕሮጀክቱ ዋና ጽሕፈት ቤት ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየአካባቢው ያሉትን የፕሮጀክቱን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በመክፈት ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።

በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው አዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ- ልማት ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ ቀጥሎ ቢሆን በዚህ ዓመት ይጠናቀቅ እንደነበር ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ እጅግ ግዙፍና ለአገራዊ ልማት መፋጠን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የተናገሩት ኢንጂኒር በሃይሉ ከፍተኛ የመንግስትና ህዝብ ኃብት የፈሰሰበትን ፕሮጀክት እውን ይሆን ዘንድ የአካባቢው ህዝብ ደህንነቱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያከናውነው "ያፒ መርከዚ" በተሰኘ የቱርክ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም