በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ጫና አጥብቀን እናወግዛለን-የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ጫና አጥብቀን እናወግዛለን-የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት የሚደረገውን ጫና አጥብቀው እንደሚቃወሙ የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክር ቤቱ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በውጭ ጣልቃ ገብነት ዙሪያ ዛሬ ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ መክረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪው ህወሃት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እና እየተከተለ ያለውን የሰላም አማራጭ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሃት በባህሪው የሰላም ፍላጎት የማይዋጥለት መሆኑን የጠቀሱት የምክር ቤቱ አባላት፤ በተለይም በየጊዜው ተቀበልኩ የሚለው የሰላም አማራጭ ጊዜ ለመግዛት የሚጠቀምበት ስልቱ መሆኑ አንሰተዋል።
ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን የሽብር ቡድን ከስር መሰረቱ በማስወገድ ሀገሪቱን ከውጭ ጫና ማላቀቅ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሀገር ጉዳይ ልዩነት እንደሌላቸውና ሀገር ከሚመራው መንግሥት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ከሌላው ጊዜ በተለየ አንድነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ የኋላእሸት በቀለ በውይይቱ ማጠቃለያ በህዝብ ትግል ከስልጣን የተወገደው አሸባሪው ህወሓት ጦርነትን መርጦ በሀገሪቱ ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ተናገረዋል።
የሽብር ቡድኑ ከታሪካዊ ጠላቶች እና ከአንዳንድ ውጭ ሀይሎች ጋር በማበር ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ጦርነት ከፍቶ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ አጥብቀን ልንታገለው ይገባል ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውንም ድርጊት አጥብቀው እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል ህዝብም መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅና ለማስከበር እየወሰደ ያለውን የመከላከል እርምጃ ከጎኑ ሆኖ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።