ቀጥታ፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ-ኤሌትሪክ ድል ቀንቷቸዋል

ጥቅምት 10 2015 (ኢዜአ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ-ኤሌትሪክ ድል ቀንቷቸዋል።

የአራተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

ኢትዮጵያ ቡና በመስፍን ታፈሰ ባስቆጠራት ግብ ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ እስካሁን አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው ሲዳማ ቡና በሊጉ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።

በሌላኛው ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌትሪክ በሄኖክ አየለ፣አብነት ደምሴና ምንያህል ተሾመ ግቦች ለገጣፎ ለገዳዲን 3 ለ 0 አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ-ኤሌትሪክ ነጥቡን ወደ አራት ከፍ በማድረግ ከነበረበት 15ኛ ደረጃ ወደ 7ኛ ከፍ ብሏል። በአንጻሩ ለገጣፎ ለገዳዲ በአራት ነጥብ ከ7ኛ ወደ 8ኛ ደረጃ ወርዷል።

ነገ ፋሲል ከነማ ከመቻል ከቀኑ 7 ሰአት እንዲሁም ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 10 ሰአት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊጉ አራተኛ ሳምንት መርሐግብር ይጠናቀቃል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ12 ነጥብ ሲመራ፤ ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም