ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከ410 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ጸደቀ

ጥቅምት 10/2015(ኢዜአ) በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ካቀረበው የበጀት ጥያቄ ውስጥ 410 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በጀት ፀድቆ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። 

በደቡብ ክልል በሚገኙት የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ ኮንሶና፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የሕዝበ ውሳኔው ድምፅ የሚሰጥበት ቀን ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለማካሄድ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።   

ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ካቀረበው የበጀት ጥያቄ ውስጥ 410 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በጀት ፀድቆለት ሥራ ጀምሯል ብለዋል።     

ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ግብዓት ለማሰባሰብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት፣ ከመንግሥት አስተዳደር፣ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች እንዲሁም ጸጥታ ተቋማት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

ምርጫውን ለማስፈጸም 18 ሺህ 750 ምርጫ አስፈጻሚዎች እንደሚያስፈልጉ የተናገሩት ሰብሳቢዋ ከዚሁ ውስጥ 9 ሺህ የሚሆኑት ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል።    

ተጨማሪ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመል በነገው ዕለት ቦርዱ በኦንላይን ማስታወቂያ እንደሚያወጣም ተናግረዋል።   

ማንኛውም ዜጋ ቦርዱ ዕጩ አድርጎ ያቀረባቸው አስፈጻሚዎች ላይ ችግር አለ ብሎ በሚያምንበት ጊዜ አስተያየት በኦንላይን ማቅረብ የሚችልበት አሰራርም ተመቻችቷል ብለዋል።

ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ አንድ ዋና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን በቀጣይም በዞኖችና ወረዳዎች ለማቋቋም እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።    

በአሁኑ ወቅት 11 ጽሕፈት ቤቶች  መቋቋም ነበረባቸው፤ ነገር ግን የአካባቢዎቹ አስተዳደሮች ለቢሮ የሚሆኑ ቦታዎችን በቶሎ ባለማዘጋጀታቸው የሚፈለገውን ያህል መጓዝ አልቻልንም ነው ያሉት።  

በምርጫው ላይ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት፣ ባለሙያዎችን የማደራጀት ሥራዎችም እንዲሁ በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

 በሕዝበ ውሳኔው ላይ ለመሳተፍ ከ 3 ሚሊዮን 106 ሺህ በላይ መራጮች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቦርዱ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም