የሚጠቅመንን መምረጥ ያለብን እኛው ነን - አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ

142

እንግዳው ከፍያው (ኢዜአ)

በባህርዳር ከተማ ሰሞኑን የተካሄደው 10ኛው የጣና ከፍተኛ የሰላምና ደህንነት ፎረም የመጨረሻው ቀን ውይይት ነፃ ውይይት፣ ንግግርና ነፃ የመፍትሄ ሃሳብ ማመንጨት የሚለውን የፎረሙን መርህ በግልፅ ያንጸባረቀ ነበር። ፎረሙ አፍሪካውያን የሚያጋጥሟቸው መሰናክሎችን አልፈው ለዕድገትና ብልፅግናቸው የሚከተሏቸውን ስልቶችና መዳረሻቸውን ያመላከቱበት ነበር ማለት ይቻላል።

ፎረሙ ምንም እንኳ የአፍሪካን የሰላምና ፀጥታ ችግሮች በነፃ ውይይት፣ ንግግርና ክርክር በራሳቸው መንገድ ለመፍታት አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት ቢሆንም፤ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገሮች እኛም አለንበት ብለው ጣልቃ ከመግባት ያገዳቸው እንዳልነበር ሂደቱ ማሳያ ነው። ለዚህም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጭምር ፍላጎታቸውን በፎረሙ ላይ አንፀባርቀዋል። ጠንከር ያሉ ሃሳቦችን ያነሱበት፣ ጥያቄዎችን  የጠየቁበትና ፍላጎታቸውን የገለጹበትም ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሃመር ምንም እንኳ ሃሳባቸው በፎሮሙ በተሳታፊዎች የገጠመው ሙግት ቀላል ባይሆንም፤ አሜሪካ ለአፍሪካ ሀገሮች ያላትን በጎ አሳቢነት፣ ድጋፍና ትብብር አንስተዋል። አምባሳደሩ የታዳሚውን ሃሳብም ሆነ የፎረሙን የአጀንዳ አቅጣጫ ለማስቀየር ያደረጉት ጥረት ባይሳካም ቅሉ ንግግራቸውን ሲጀምሩ ፎረሙ ከሚካሄድበት በቅርብ ርቀት ላይ ሰው እየሞተ፣ እየተራበ፣ እየተሰደደና እየተሰቃየ ነው ሲሉ የመንግሥታቸውን የተለመደ ሃሳብ አቅርበዋል። ችግሩን ለመፍታት የአሜሪካ መንግሥት አቋም መጀመሪያ ተኩስ መቆም አለበት የሚል ነው ሲሉም አከሉ፤ አሸባሪው ህወሓት ሀገር የማፍረስ የቀን ቅዥቱ አልሰምር ሲለው የሚመዟትን የተለመደችውን የመጠባበቂያ ካርድ መዘው ድምጻቸውን አሰምተዋል፤ ሰሚ ጆሮ ባያገኙም ቅሉ።

አምባሳደር ሃመር እንደ አሜሪካ ለአፍሪካ በሰብዓዊ እርዳታ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ ድጋፍ ያደረገ የለም፤ ካለ መጥቀስ ይቻላል፤ አፍሪካውያን ዴሞክራሲን በመተግበር ለህዝባችሁ ታማኝ መሆን አለባችሁ ሲሉም ትእዛዝ መሰል መልዕክትም አስተላልፈዋል። አክለውም “ማንም ሀገር ራሱን ችሎ መቆምም ሆነ ማደግ አይችልም” የሚል እምነት ስላለን ነው ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ድጋፍ የምናደርገው አሉ። “የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት እናከብራለን” መሪዎችም ለህዝባቸሁ ኃላፊነት ያላቸሁ መሆን አለባችሁ ሲሉ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጥያቄ መልክ አቀረቡ አምባሳደር ሃመር ።

በአምባሳደር ሃመር ንግግር ስሜት ውስጥ የገቡ የመሰሉት በፎረሙ ከታደሙ ምሁራን መካከል በፓን አፍሪካ አቀንቃኝነታቸውና በአነቃቂ ንግግራቸው የሚታወቁት ኬንያዊ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ ምዕራባውያን “አፍሪካውያን ራሳችንን ችለን እንድንቆም ተውን” የሚል አጭር  መልዕክት አስተላለፉ። ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ተነስተው ዴሞክራሲ…ዴሞክራሲ እያላችሁ አፍሪካውያንን ትጨቀጭቃላችሁ! ነገር ግን በሀገራችሁ ጥቁር አሜሪካውያን እስካሁን ከነጮች ጋር እኩል መብት የላቸውም! ዴሞክራሲ ከተባለ መጀመሪያ የራሳችሁን አስተካክላችሁ ነው እኛን መስበክ ያለባችሁ! የሚል ይዘት ያለው ሃሳብ ሰነዘሩ።

የቀድሞው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር የሚደርጉበት ሰዓት ደረሰና ከአምባሳደር ማይክ ሃመርና ሌሎች ነጮች ለተነሳላቸው ጥያቄ አዘል አስተያየት መልስ ለመስጠት ማይካቸውን ሲያነሱ የፎረሙ ተሳታፊዎች ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ እሳቸው አድርገው የሚሉትን ለማድመት በጉጉት ይጠባበቁ ጀመረ።

አቶ ኃይለማርያም ንግግራቸውን  "ለአፍሪካ እንደ አሜሪካ ድጋፍ ያደረገ ሀገር የለም፤ ባሉት ጉዳይ እኔም እስማማለሁ" ሲሉ ጀመሩ። ይህን ጊዜ አምባሳደር ማይክ ሃመርም ደጋፊ አገኘሁ በሚል ኮራ ብለው ሙሉ ትኩረታቸውን አቶ ኃይለማርያም ላይ አደረጉ። አቶ ኃይለማርያም አከሉ ሀገሬ ኢትዮጵያን ለ40 ዓመታት ብዙ ቢሊዮን ዶላር አውጥታ በድርቅ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም ባደረገችው ሁለንተናው እንቅስቃሴ የስንዴ ድጋፍ አድርጋችኋል አሉ።  ነገር ግን ካደረጋችሁት በበዙ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ውስጥ ትንሽ ሚሊዮን ዶላሩን ቀንሳችሁ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በምናደርገው ጥረት ላይ አውላችሁት ቢሆን ኖሮ እንኳን ለራሳችን ሕዝብ ለሌላም የሚተርፍ ምርት ማምረት እንችል ነበር ሲሉ በአጽዕኖት ተናገሩ። በዚህን ጊዜ የአምባሳደር ማይክ ሃመር ስሜት የተረበሸ መሰለ። አቶ ኃይለማርያም ግን ንግግራቸውን ሳይገቱ ቀጠሉ፤ የስንዴ ድጋፍ የምታደርጉት እኮ በሌላ መንገድ ሲታይ ለምርታቸሁ የገበያ አማራጭ አድርጋችሁ ስለምትጠቀሙበት ነው፤ ሲሉ ሙግቱን አከረሩት። ድርቅ የሚከሰተው በእናንተ ኢንዱስትሪዎች ምክንያት በተፈጠረ አየር መዛባት ነው ህዝባችን ችግር ውስጥ እየገባ ያለው አሉ።

አሁን ላይ በራሽያና ዩክሬን በተፈጠረው ግጭት ዩክሬንን እያነሳችሁ ለአፍሪካ ስንዴ የሚመጣው ከዩክሬን ነበር፤ በጦርነቱ ተስተጓጎለ ትሉናላችሁ፤ ይህን እኛም ለምን? ብለን መጠየቅ አለብን። በዓለም ላይ ለእርሻ ተስማሚ ከሆነው መሬት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በአፍሪካ ነው። አሜሪካና አጋሮቿ ኢትዮጵያን፣ዝምባቤዌን፣ ታዛንኒያን፣ ሱዳንና ማላዊን ስንዴ እንዲያመርቱ የግብርናውን ዘርፍ ብትደግፉ አፍሪካ በምግብ ራሷን እንድትችል ማድረግ ይቻላል። በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ይህን ሃሳብ አንስቼ ስሞግት የተሰጠኝ መልስ በጣም አስገራሚ ነበር ሲሉ በአግራሞት ገጠመኛቸውን እንዲ ብለው ነበር ያስታወሱት። “የእኛ ፖሊሲ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ነው” የሚል ነበር የተሰጠኝ መልስ አሉ አቶ ኃይለማርያም፤ ንግግራቸው  በታዳሚው ጭብጨባ እንደ ደመቀ ቀጠለ።

አምባሳደር ሃመር እንዲያውቁት የምፈልገው ነገር እርዳታ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አጋርነትን አያረጋግጥም። ይልቁንም በረጅና በተረጅነት መካከል ኢ-ፍትሃዊነትን የሚያነግስ ነው። በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አጋርነትን ለማስፈን አፍሪካውያን በራሳችን የተሰራ የራሳችን ፖሊሲ ያስፈልገናል፤ ራሳችንን ችለን በመቆም ለመደራደር የሚያስችል አቅም መፍጠር ይገባናል ያልኩት ለዚህ ነው ሲሉ ሀቁን አስረግጠው አስረዱ  አቶ ኃይለማርያም።

አቶ ኃይለማርያም አከሉ ምዕራባውያን ከቻይና ጋር ባለን ግኙነት ደስተኛ አለመሆናቸው ሌላው ጉዳይ ነው አሉ። አሁን ላይ እኛ አፍሪካውያን ከቻይና በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በመሰረተ ልማት ግንባታ ብዙ ጥቅም እያገኘን ነው። ነገር ግን እናንተ በዚህ ደስተኛ አይደላችሁም። ለአብነትም ኢትዮጵያ  የባሕር በር የሌላት በመሆኗ የባቡር አዲድ መስመር በእጅጉ ያስፈልጋታል። ከጅቡቲ አዲስ አባባ ያለውን የባቡር መንገድ/ሀዲድ እንድንዘረጋ ቻይና ናት የገንዘብ ድጋፍ ያደረገችልን። የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ስንገነባ የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ቢሮዬ ድረስ መጥተው ባደረግነው ውይይት “ከቻይና ጋር እስከዚህ የሚያደርስ ግንኙነት የመሰረታችሁት ለምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውኝ ነበር።  እኔም “ኑና የባቡር ሀዲድ ግንባታው ላይ ኢንቨስት አድርጉ፤ ያኔ እኔ ወደ ፈረንሳይ አመጣለሁ” አልኳቸው ሲሉ አቶ ኃይለማርያም የፎረሙ ታዳሚዎች አዳራሹን በጭበጫባ አደመቁት።

አሜሪካና አጋሮቿም የአፍሪካ ሀገራሮችን ከእርዳታ ይልቅ በኢንቨስትመንት መደገፍ አለባቸው። ባለሃብቶቻችሁ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ። ለማንኛውም የሚጠቅመንን የምናውቀው እኛ ነን፤ የሚጠቅመንን መምረጥ ያለብንም እኛው መሆናችን ሊታወቅ ይገባል፤ አሉ ፈርጠም ብለው አቶ ኃይለማርያም ።

ዴሞክራሲ ከማስፈን ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄም የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ የህይወት ዘመናቸውን ሙሉ የቻይና መሪ ሆነው ቢዘልቁ የቻይና ጉዳይ እንጂ የእኛ የአፍሪካውያን ጉዳይ አይደለም። የአሜሪካ ዴሞክራሲም ለራሳቸው የጠቀመና ተስማሚ ቢሆን የአሜሪካ እንጂ የእኛ ጉዳይ አይደለም። ይህን በአግባቡ መረዳት ይገባል። ዴሞክራሲ ወደ እኛ ሲመጣ ግን ከባህላችን፣ እሴታችንና ከህዝባችን ፍላጎት ጋር በማጣጣም መተግበር ግድ ይለናል ማለት ነው።

እንደሚታወቀው እኛ የአፍሪካ ሕብረትን ትራንስፎርም ለማድረግ በነፃ ውይይት ሃሳብ ለማመንጨት በማለም የዛሬ 10 ዓመት ገደማ የጣና ሰላምና ደህንነት ፎረምን መስርተን መንቀሳቀስ ጀመርን። ወዲያውኑ ፈረንሳይ አክራ ላይ የሚካሄድ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ላይ የሚወያይ ተመሳሳይ ፎረም መሰረተች። አያችሁ! ይሄ ጉዳይ የአፍሪካን ጉዳይ ከእነሱ እውቅና ውጭ ምንም አይነት ውይይት፣ ንግግርና ክርክር እንዳይካሄድ ከመፈለግ የመነጨ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው።

"ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ተወቃሽ የማደርገው ራሳችን እንጂ እነሱን አይደለም። እንደፈለጉ እንዲያደርጉን እኛ ፈቅደንና ወደን የሰጠናቸው ስጦታ አድርጌ ነው የምቆጥረው። አሁን ላይ ቤታችን የሆነችውን አፍሪካን ማሟሟቅ ግድ ከሚለን ወቅት ላይ እንገኛለን። የአየር ንብረትን ጨምሮ በሚገጥሙን ጉዳዮች ላይ ራሳችን ለብቻችን መነጋገር፣ መወያየት፣ መመካከርና የመፍትሄ አቅጣጫ እያስቀመጥን መስራት አለብን ብዬ አስባለሁ። ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የራሳችን ፈንድ ማሳደግ አለብን። በህገወጥ መንገድ የሚወጣውን ዶላር መቆጣጠር፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መግታትና ሌሎች ችግሮችን መቅረፍ አለብን" ሲሉ ነው አቶ ኃይለማርያም ያስገነዘቡት።

ለዚህም የአፍሪካውያን ዋና ችግር  ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ማየታቸው ነው። ይህ የሚመነጨው ደግሞ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አለመውጣትን ነው። እኛ አፍሪካውያን ራሳችንን ዝቅ የሚያደርገን ምንም ምክንያት እንደሌለ ታሪካችን ማሳያ ነው። ለዚህ የአፍሪካን ስልጣኔ መመልከት ተገቢ ነው። በኢትዮጵያ የአክሱማውያን ስልጣኔ፣ በግብፅ የሚሶፖታኒያን ስልጣኔና ሌሎች ማሳያ ናቸው። በዓለም ላይ የመጀመሪያው መድኃኒት የተቀመመው በግብፆች ነው። አስትሮኖሚ፣ ሂሳብ፣ ኢንጅነሪንግና ሌሎች ስልጣኔዎች መጀመሪያ እኛው አፍሪካውያን መሆናቸውን ማስታወስ በቂ ነው።

ይህን ታሪካችንን ለልጆቻችን ለማስተማር፣ ተቋማትን ለመገንባት፣ ወጣት አመራሮችን በማሰልጠን ለማዘጋጀትና ባህልና ታሪካችንን ለማሳወቅ እንደ ጣና ፎረም ያለ አማራጭ የለም። አጋሮቻችንም በፎረሙ የምንደርስበትን ድምዳሜ ወደ ተግባር ለመቀየር በምናደርገው ርብርብ በፈለግነው መንገድ ድጋፍ ሊያደርጉልን ይገባል እንጂ ሊወስኑልን መፍቀድ የለብንም።

በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ከ5 ሺህ በላይ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ንግሥት ሳባ ወደ እስራኤል ተጉዛ ጥበብን ከሰሎሞን ስትቀስም አሜሪካ የምትባል ሀገር አልነበረችም፤ አትታወቅም፤ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትም እንዲሁ። አሁን ላይ የብዙ ሺህ ዘመን ታሪካችንን በመዘንጋት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ስለ ሀገር መፍረስ ሲነግሩን ያሳፍራል።  አሁን ከአጋሮቻችን ጋር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመፍጠር ከዝቅተኝነትና ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መውጣት አለብን። ለዚህ ደግሞ ታላቁ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን አርዓያችን ማድረግ ይገባናል። የእሳቸውን ፈለግ ተከትለን አፍሪካን ማሻገር እንችላለን።

“የኛ አርበኝነት መሰረቱ ታሪካችን መሆኑንም መዘንጋት የለብንም”። በአፍሪካ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ወደ ራሳችን ወስደን፣ ችግሩን መርምረን፣ የመፍትሄ አቅጣጫ ቀይሰን በቁርጠኝነት ከሰራን የአፍሪካን እድገት በማረጋገጥ የተረጅነት ታሪካችንን የማንቀይርበት ምንም ምክንያት የለም" ብለው አቶ ኃይለማርያም ንግግራቸውን ሲቋጩ የፎረሙ ተሳታፊዎች ከልብ የመነጨ አድናቆታቸውን በጋለ ጭብጨባ ገልጸውላቸዋል።

"ለማንኛውም የሚጠቅመንን የምናውቀው እኛ ነን፤ የሚጠቅመንን መምረጥ ያለብንም እኛው ነን" ሲሉ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በንግግራቸው አጽዕኖት የሰጡትን አብይ ጉዳይ  የ10ኛው የጣና ከፍተኛ የሰላምና ደህንነት ፎረም ታዳሚዎችን ልብ ያለው ልብ ይበል ያሰኘ፤ አፍሪካውያን የሚያስፈልጋችሁን የምናውቅላቸሁ እኛ ነን፤ በውስጥ ጉዳያቸሁ ገብተን ካልፈተፈትን ለሚሉ አንዳንድ ምዕራባዊያን ደግሞ ቆም ብለው ደግመው ደጋግመው እንዲያስቡ ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈና ትምህርት የሰጠ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም