ቀጥታ፡

የዲጅታል መታወቂያን ስራ ላይ ማዋል የተለያዩ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል- የምክር ቤት አባላት

ጥቅምት 10/2015 (ኢዜአ) የዲጅታል መታወቂያን ስራ ላይ ማዋል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል የጎላ ፋይዳ እንዳለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

ኢትዮጵያ በአለም ላይ ካሉ 193 የተባበሩት መንግስታት አባል አገሮች መካከል ዘመናዊ የዲጂታል መታወቂያ ስርአት ከሌላቸው 47 አገሮች አንዷ መሆኗ ተገልጿል።

በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያገለግል ወጥ፣ አስተማማኝና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ የዲጅታል መታወቂያ ስርአት አለመኖር ዜጎችን ከሌሎች  ግለሰቦች በልዩ ሁኔታ ለመለየት አልተቻለም።

ይህም አንድ ሰው በተለያየ ስምና ማንነት በርካታ መታወቂያዎችን በመያዝ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እንዲሳተፉ እድል ፈጥሯል።

በመሆኑም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለጸገ መሰረታዊ የዲጂታል መታወቂያ ስርአት መዘርጋት ማስፈለጉን በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል።

የዲጂታል መታወቂያ ስርአት መዘርጋት አገራዊ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ ልማትን በአግባቡ ለማቀድ፣ የምጣኔ ሃብት ሽግግርን ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይገልጻል።

በማህበራዊና ምጣኔ ሃብት የልማት ስራዎች የአካታችነት ችግሮችን በቀላሉ በመለየት በነዋሪዎች መካከል ፍትሃዊነትን ለማስፈንና ከወንጀል ጋር የተያያዙ ስጋቶችን በመቀነስ አገራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስርአትን ለመዘርጋት አዋጁን ማውጣት አስፈልጓል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፤ ዲጀታል መታወቂያ ዜጎችን በግልጽ በማወቅ ለአገርና ህዝብ ደህንነት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አብራርተዋል።

ሙሉ ስም፣ የትውልድ ቀን፣ ወርና አመት፣ ጾታና የመኖሪያ አድራሻ የዲጅታል መታወቂያ ስርአት የሚያካትታቸው መረጃዎች ሲሆኑ ዜግነት፣ ስልክ ቁጥር ኢሜል ና የፖስታ ቁጥር እና ሌሎች ጥንቃቄ የሚፈልጉ መረጃዎችን በአማራጭነት ሊይዝ እንደሚችል አዋጁ ይደነግጋል።

የዲጅታል መታወቂያን ስራ ላይ ማዋል ሙስናን ጨምሮ የተለያዩ የወንጀል ተግባራትን በመከላከል ለአገር ሰላምና ደህንነት አስፈላጊ መሆኑን የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተካተቱ ትርጓሜዎች፣ መረጃዎችና አገላለጾች ላይ በትኩረት መታየት ያለባቸውን ጉዳዮችም አንስተዋል።

ምክር ቤቱ የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት መርምሮ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ የተነሱ ጥያቄና አስተያየቶችን ጨምሮ በዝርዝር እንዲታዩ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት፣ ለሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተመሳሳይ ስለ እጽዋት ዘር ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅና የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል።

የቀረቡ ረቂቅ አዋጆች የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ከማሳደግ፣ የአርሶ አደርና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ከመጨመር አኳያ ያላቸው ፋይዳ ላይ በመወያየት የተነሱ ጥያቄና አስተያየቶችን ጨምሮ በዝርዝር እንዲያየው ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው በህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ እና በፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ላይ ያለውን የስራ ጫና ለመቀነስ የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀትን ለማሻሻል የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቅል።

በዚህም 10 ተቋማትን የሚከታተል የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና 35 ተቋማትን የሚከታተል የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ በማደራጀት በምክር ቤቱ የነበሩት 11 ቋሚ ኮሚቴዎች 13 ሆነው ተደራጅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም