ቀጥታ፡

የአንዳንድ ምዕራባውያን አገራትን ጣልቃ ገብነትና ጫና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በብራሰልስ እየተካሄደ ነው

ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና ጫና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በቤልጂየም ብራሰልስ በመካሄድ ላይ ነው።

በአውሮፓ ኮሚሽን ፊት ፊት በሚገኘው ሹማን አደባባይ እየተካሄደ በሚገኘው ሰልፍ በአውሮፓ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስና ጀርመን ዳያስፖራዎቹ ጣልቃ ገብነቱን በመቃወም ሰልፍ ከመጡባቸው አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ሰልፉ ዓላማ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በመቃወም ነባራዊ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሆነ ኢዜአ ከ‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ’ የብራሰልስ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሰልፈኞቹ አንዳንድ ምዕራባዊ አገራትና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንዲያቆሙና እጃቸውን እንዲያነሱ የሚያስገነዝቡ መፈክሮችን እያሰሙ ይገኛሉ።

የሰልፉ አስተባባሪዎች የአውሮፓ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ላይ እየደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ደብዳቤ ለኮሚሽኑ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ አቅርበዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ የሚከናወንበት ሹማን አደባባይ ከኮሚሽኑ በተጨማሪ የቤልጂየም ፓርላማ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ እና ሌሎችም ትላልቅ የመንግስት ተቋማት የሚገኙበት ነው።

‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ’ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በማስተባበር በዲጂታል ምህዳሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በትዊተር የተለያዩ መልዕክቶችን በመቅረጽ ዘመቻ እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም