ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ

መተማ ጥቅምት 10/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው መተማ ወረዳ ለሚገኙ ወገኖች የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

የማህበሩ የመተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ግዛቸው በለጠ እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ 330 ወገኖች ነው።

ድጋፉ የተፈናቃይ ወገኖች የዕለት ችግር ለመፍታት ታስቦ የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማህበሩ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልፀዋል።

ተፈናቃይ ወገኖች ያሉበትን ችግር በመረዳት በቋሚነት እስኪቋቋሙ ድረስ ሌሎች ድርጅቶችም ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከተጠቃሚዎች መካከል አቶ የቻለ መንጌ ''የዞኑ ምግብ ዋስትና በየወሩ 15 ኪሎ ግራም ስንዴ ያግዘናል ለህክምናና ሌሎች ወጭዎችም የቀይ መስቀል ማህበር ያደረገልን የ4 ሺህ ብር ድጋፍ ያግዘናል ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ በበኩላቸው አሁን ለሁለተኛ ጊዜ 6 ሺህ 600 ብር ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በዘላቂነት ሊያቋቁመን ይግባል ሲሉም ጠይቀዋል።

የዞኑ ምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ዘላለም አበበ እንደተናገሩት በዞኑ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች አሉ።

የተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከተረጂዎች ቁጥር አንፃር በተገቢው መንገድ ተደራሽ ለማድረግ አዳጋች መሆኑንም አንስተዋል።

ክልሉ ከሚሰጠው የስንዴ ድጋፍ እና ከቀይ መስቀል ውጭ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም መሰል ድጋፍ በማድረግ ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት ሊቋቋሙ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም