የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲ መሰጠት መጀመሩ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዛል- የትምህርት ጥራት ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲ መሰጠት መጀመሩ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዛል- የትምህርት ጥራት ባለሙያዎች
ጥቅምት 10 /2015 (ኢዜአ) የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲ መሰጠት መጀመሩ የትምህርት ጥራት ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ የትምህርት ጥራት ባለሙያዎች ገለጹ።
በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ የጥራት ጉድለቶችን ለማስተካከል አዲስ ሥርዓተ- ትምህርት በመቅረጽ ጭምር የጥራት ማስጠበቅ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ያለው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የጥራት ማስጠበቅ ሂደቱ አጋዥ ተግባር መሆኑን ተገልጿል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች፤ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ያለው ብሄራዊ ፈተና ኩረጃንና የፈተና ሥርቆትን ለማስቀረት እንዲሁም በአስተማማኝ ጸጥታ ለመፈተን የላቀ ሚና እንዳለው ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ሙያ ብቃት ምዘና ቡድን መሪ ሰንደቁ ያዛቸው፤ የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ መደረጉ ለትምህረት ጥራት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው የትምህርት ጥራት ባለሙያ መስፍን ተክለማርያም፤ ኢትዮጵያ በትምህርት ተደራሽነት ላይ አመርቂ ውጤት ብታስመዘግብም በትምህርት ጥራት ላይ ግን ችግሮች መስተዋላቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት አሁን የተጀመሩ ስራዎች ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
በ12ኛ ክፍል የተጀመረው ጥብቅ የምዘና ስርዓት ከታች ጀምሮ ሊተገበር እንደሚገባ ጠቁመው በተለይም ወላጆች፣ መምህራንና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ምዘናው በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚመጡ ተፅዕኖዎች የራቀ ስለሚሆን በራሳቸው ጥረት የሚሰሩ ተማሪዎች ውጤታቸውን አግኝተው ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድላቸውን ያሰፋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ፈተናዎች ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆኑ የቴክኖሎጂ አሰራሮች ሊሰጡ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።