አዲስ አበባ ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ በሰራችው ስራ በአለም አቀፍ ውድድር አሸናፊ ሆነች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ በሰራችው ስራ በአለም አቀፍ ውድድር አሸናፊ ሆነች
ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) አዲስ አበባ ከተማ የበካይ ጋዝን በሚያስቀር ዘመናዊ ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በመዘርጋት ባከናወነችው መልካም ስራ በC40 የከንቲባዎች ፎረም አለም አቀፍ ውድድር አሸናፊ ሆነች።
ሽልማቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ከጥቅምት 9 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከተማ እየተካሄደ ባለው የC40 የአለም ከንቲባዎች ፎረም ላይ የአየር ንብረትን የሚከላከል ተስማሚና መልሶ የመጠቀም አሰራርን የተገበረ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በመዘርጋት ለአረንጓዴ እና ጤናማ የከተማ ግንባታ ሂደት እና ቆሻሻን ወደ ኮምፖስት በመቀየር ለገቢ ማስገኛ ስራ በማዋልዋ ጉልህ ድርሻ በማበርከት በመልካም ተሞክሮ ተሸላሚ መሆን ችላለች፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም የነበረውን ለበካይነት የተጋለጠ አሰራር በማስቀረት በቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የብዙዎችን ህይወት ሊታደረግ የሚችል እና የበካይ ጋዝ ልቀትን ያስቀረ፣ ተመልሶ በከተማ እየተከናወነ ላለው የጓሮ አትክልት ልማት ስራ ማዳበርያ ማቅረብ ያስቻለ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት መዘርጋቱ ለእውቅና እንዳበቃው ተጠቅሷል፡፡
በዚህም ስራ በርካታ ወጣቶች ገቢያቸውን በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደጉም በተጨማሪ ተፈጥሮን የሚያክም ቆሻሻን ወደ ሃብትነት የቀየረ በመሆኑ ከብዙ ትላልቅ የዓለም ከተሞች ከቀረቡ ተሞክሮዎች ጋር በመወዳደር አዲስ አበባ አሸናፊ በመሆኗ ሽልማቱን ማግኘት መቻሏን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።
የC40 የአለም ከንቲባዎች ፎረም ከተሞች የአየር ንብረት ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት እና ለአለም ከተሞች የሙቀት መጨመር ምክንያት ሆነው ግሪንሃውስ ጋዝ ተፅእኖ በጋራ ለመከላከል የተመሰረተ የአለም ሀገሮች 100 ዋና ከተሞች ጥምረት የተመሰረተ ነው፡፡
አዲስ አበባ ከቀናት በፊት በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ የእውቅና ሽልማት ማግኘቷ አይዘነጋም፡፡