ቀጥታ፡

ዳያስፖራው ለተፈናቀሉ ወገኖች ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) ዳያስፖራው አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለወገናቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርቧል።

መንግስት ዳያስፖራው ለአገሩ በአንድ ማዕከል ድጋፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከቻፓ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር ‘አይዞን ኢትዮጵያ’ የተሰኘ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጭ አልምተው ወደ ስራ ማስገባታቸውን ገልጿል።

ከጥቅምት እስከ ጥር 2014 ዓ.ም ድረስ በተካሄደ የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ በመተግበሪያው ስድስት ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በባንክ ዝውውር አንድ ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡና ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን መተላለፉን አመልክቷል።

ኮሚሽኑም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተገኘውን ሰባት ሚሊዮን ዶላር በመጠቀም በአማራና በአፋር ክልሎች ለሚገኙ 699 ሺህ 870 በላይ የተፈናቀሉ ወገኖች ብር ከ349 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 105 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምግብ ነክ አቅርቦት ማከፋፈሉን ለአገልግሎቱ በላከው መረጃ ማሳወቁን ጠቅሷል።

መንግስት ሶስተኛው ዙር ወረራን ተከትሎ ድጋፍ የሚፈልጉ በርካታ ወገኖች መኖራቸውን ተከትሎ ዳያስፖራው ድጋፍ እንዲያደርግ ባቀረበው ጥሪ መሰረት እስካሁን በአይነት የተደረገውን ድጋፍ ሳይጨምር ወደ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት እንደተሰባሰበ አመልክቷል።

በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአይዞን ኢትዮጵያ አማራጭ እና ለድጋፍ የተዘጋጁ የባንክ የሂሳብ ቁጥሮችን በመጠቀም የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም