ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን 500 ሺህ ኩንታል የቅባት እህል ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ

አምቦ፣ ጥቅምት 10/2015(ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኸር ወቅት ከተዘራው የቅባት እህል 500 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በዞኑ በመኸር ወቅት ከ44 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቅባት እህል መሸፈኑም ተገልጿል።

በቅባት እህል እየተሳተፉ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል የአምቦ ወረዳው አርሶ አደር ቶለሳ ቀልቤሳ፤ ከምግብ ሰብል በተጓዳኝ በገበያ አዋጭ የሆነ የቅባት እህል እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በኑግና ተልባ ምርት ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከሽያጩ በአገኙት ገቢም የመኖሪያ ቤት መስራታቸውን እንዲሁም ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ በመግዛት ኑሯቸውን ማሻሻል እንደቻሉ ነው የገለጹት።

በመኸር እርሻውም በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ተልባ መዝራታቸውን ገልጸው ከዚህም አምስት ኩንታል ምርት ይጠብቃሉ።

አርሶ አደሮቹ በግብርና ባለሞያዎች ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የገለጹት።

የምዕራብ ሸዋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የአዝዕርት ልማት ባለሙያው አቶ ገዛሀኝ ዲንሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ45 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቅባት እህል ልማት እየተሳተፉ ነው።

በዞኑ እየለማ ካለ የቅባት እህሎች መካከል ኑግ፣ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ ጎመንዘርና ለውዝ በስፋት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

በግብርና ምርምር ማዕከላት የተሻሻሉ የቅባት እህል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓልም ብለዋል።

የቅባት እህል ልማቱ የምግብ ዘይት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

የግብርና ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በአማካይ ከአንድ ሔክታር 10 ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በዞኑ 500 ሺህ ኩንታል የቅባት እህል ምርት እንደሚጠበቅ ባለሙያው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም