ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሶስት ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሶስት ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ
ጥቅምት 10 ቀን 2015(ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሶስት ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ።
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ስለ እጽዋት ዘር ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን፣ የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነት ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት ለሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለዝርዝር እይታ መርቷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ለማሻሻል የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብም መርምሮ አጽድቋል።
በዚህም መሰረት የቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር ከ11 ወደ 13 ከፍ እንዲል ተደርጓል።