በአሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት የተፈፀመበት አዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ- ልማት ግንባታ ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት የተፈፀመበት አዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ- ልማት ግንባታ ሊጀመር ነው
ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት የተፈፀመበትና ግንባታው ተቋርጦ የቆየው አዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ- ልማት ግንባታ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር በኃይሉ ስንታየሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ 390 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ፕሮጀክት ሀብት የሆኑ ልዩ ልዩ ንብረቶች በአሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት የተፈጸመበት መሆኑን ገልጸዋል።
የደረሰውን ጥፋት መጠን ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ኮንትራክተሩ በተለያየ መንገድ የተረፈውን ንብረት እንዲረከብ እና አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ግንባታ መቀጠል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ንግግር ተጀምሯል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮምቦልቻ የሚገኘውን የፕሮጀክቱ ዋና ጽሕፈት ቤት ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከኮንትራክተሩም ጋር አስፈላጊውን ንግግር በማድረግ እና በየአካባቢው ያሉትንም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹን በመክፈት ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሸባሪው ህወሓት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በየቦታው የበተናቸውን ንብረቶች የመሰብሰብ ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።
በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው የወልድያ መቀሌ እና አዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ- ልማት ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ ቀጥሎ ቢሆን በዚህ ዓመት ይጠናቀቅ እንደነበር ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያከናውነው "ያፒ መርከዚ" በተሰኘ የቱርክ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው።