ቀጥታ፡

የአገር ዕድገት መሰረትና የአንድነታችን ማሳያ ለሆነው ሕዳሴ ግድብ ድጋፍና ትብብራችን ይቀጥላል- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት

ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአገር ዕድገት መሰረትና የአንድነታችን ማሳያ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍና ትብብራችን ይቀጥላል ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገኘት የግንባታውን ሂደትና አሁናዊ ገጽታ ጎብኝተዋል።

የሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማሰሪያ የአብሮነታችን ማጠናከሪያ በመሆኑ የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን ለፍጻሜ ለማብቃት በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

ግድቡ ከፖለቲካ በላይ የሆነ የአገር ሃብት መሆኑን በመግለጽ፤ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑንም ነው የገለጹት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገር አንድነት፣ ለሰላም መስፈንና ለልማት መረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ለግድቡ ግንባታ ስኬት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው በመንግሥት በኩል የታየው ቁርጠኝነትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የአገር ዕድገት መሰረትና የአንድነታችን ማሳያ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍና ትብብራችን ይቀጥላል ያሉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ግድቡን የመጎብኘት ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

የብሔራዊ ምልክት በሆኑ ጉዳዮችና በአገር ልማት ላይ ማተኮር ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠርም አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልድ ቅርስ መሆኑን የሚናገሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ፤ ግድቡ የሁላችንም በመሆኑ ግንባታውን በጋራ ማሳካት ይኖርብናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ጉብኝቱን የመሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ የሕዳሴ ግድብ የሁሉም አሻራ ያረፈበት የኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሃብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በሰላም ሥራዎችና በልማት ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ እንሰራለንም ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን ለአገር ጥቅም በጋራ መቆም አለብን" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ግድቡን መጎብኘታቸው በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ በጋራ ለመቆማቸው ዋነኛ ማሳያ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

"ኢትዮጵያ ለሁላችንም የሚበቃና ለሌሎችም የሚተርፍ ሃብት ያላት አገር ነች" ያሉት ዶክተር ዓለሙ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚሰሩ የውጭ ጠላቶች የሚላላኩ የፖለቲካ ኃይሎች ከእኩይ ዓላማቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።

የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉብኝት ከ50 በላይ ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም