ቀጥታ፡

በሰብል ስብሰባ ለበርካታ ወገኖች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል-የዞኑ ስራና ስልጠና መምሪያ

መተማ ጥቅምት 10/2015 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር የለማውን ሰብል ለመሰብሰብ ከ860 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በጉልበት ስራ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ ስራና ስልጠና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደረሰ አዱኛ እንደተናገሩት በዚህ የመኽር ወቅት ሰሊጥን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎች በ449 ሺህ ሄክታር መሬት በአርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ለምቷል።

የለማውን ሰብል ለመሰብሰብ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሰራተኛ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ከ860 ሺህ በላይ የጉልበት ሰራተኛ ወደ አካባቢው በመምጣት በስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

የጉልበት ሰራተኞቹ በምዕራብ አርማጭሆ፣ መተማ፣ በቋራና ሌሎች ወረዳዎች የተሰማሩ ሲሆን የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወገኖችም በአሁኑ ወቅት ሰሊጥና ማሾ እየሰበሰቡ ለአኩሪ አተር፣ ማሽላና ጥጥ ሰብሎች ደግሞ የእንክብካቤ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የተፈጠረው የስራ ዕድልም እስከ ጥር ወር መጨረሻ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመኸር ሰብል ስብሰባ በኋላም ለቀጣይ የመኽር ዝግጅት በማሳ ዝግጅት ስራው የሚቀጥል እንደሆነም አስታውቀዋል።

የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ጥላሁን ንጉሴ እንዳለው ከሁለት ሳምንት በፊት ከሚኖርበት አካባቢ ደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ በመምጣት በሰሊጥ አጨዳ ስራ ተሰማርቷል።

በአጨዳ እንቅስቃሴውም "በቁርጥ ስራ እስከ 700 ብር አገኛለሁ" ያለው ወጣቱ፤ ይህ ገቢም ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን መደጎም የሚያስችለው መሆኑን ተናግሯል።

ሌላኛው ወጣት አክሊሉ እሸቱ በበኩሉ ከሐምሌ 21 ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ በማሳ በማረምና ተባይ ቁጥጥር ስራ ላይ መሰማራቱን አስታውቋል።

ከመስከረም16 ጀምሮ ደግሞ በሰሊጥ አጨዳ የስራ ዕድል የተፈጠረለት መሆኑን ጠቅሶ፤ በቀን በቁርጥ ስራ እስከ 840 ብር ድረስ እያገኘ እንደሆነም ገልጿል።

በባለሃብቶችና አርሶ አደሮች የምግብ አገልግሎት እያገኘ በመሆኑ ከ20 ሺህ ብር በላይ መቆጠብ እንደቻለም ተናግሯል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች ስብሰባ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ታውቋል።

በተያዘው የመኽር ወቅት በዞኑ ከ449 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲሆን ከዚህም ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም