ቀጥታ፡

አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት መደረጉ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም- የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ጥቅምት 10/2015/ኢዜአ/የበርካታ ህዝብ መኖሪያና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነችውን አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት መደረጉ አሁንም የቅኝ ግዛት ስሜቱ እንዳለ ማሳያ መሆኑን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ ከ15 የአፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ-ምልልስ አድርገዋል።

የአፍሪካና የእስያ ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራቸው መደረጉ ፍትሃዊነት የጎደለውና ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

በርካታ የሕዝብ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሀብትና ለዓለም ኢኮኖሚ የጎላ አበርክቶ ያላት አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ኖሯት የራሷን ድምፅ ማሰማት የምትችልበት ዕድል መኖር አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

አፍሪካ የራሷ ጉዳዮች ውሳኔ በሚሰጥበት ታላቅ መድረክ ላይ የዳር ተመልካች መሆኗ በፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ላይ አሁንም የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እንዳለ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ሩሲያ "አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል" የሚል ፅኑ አቋም እንዳላትም ነው የገለጹት ቃል-አቀባይዋ።

በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ከሚከሰቱ ግጭቶች አብዛኛው ቅኝ ገዥዎች ትተውት ባለፉት የጠብና ግጭት ምክንያቶች መሆኑንም አብራርተዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ የሚከሰቱ ችግሮችን አፍሪካዊያን በራሳቸው የመፍታት አቅም ስላላቸው ይኸው ነፃነታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካዊያንን ጉዳዮች በራሱ አቅምና በነጻነት መፍታት የሚችል ተቋም መሆኑን ሩሲያ ታምናለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም