ምክር ቤቱ በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይወያያል - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይወያያል
ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች የተያዙ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።
የዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች መሰረታዊ የግለሰብ ስነ-ሕዝብ /ዲሞግራፊክ/ እና ተፈጥሯዊ የሆኑ የዓይን፣ የጣትና የፊት የባዮሜትሪክ መረጃዎችን መዝግቦ በማዕከላዊ ቋት የሚይዝ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተደንግጓል።
ማንኛውም ነዋሪ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ካከናወነ በኋላ ልዩ ቁጥር በመስጠት የተደራጀ እና አስተማማኝ የዲጂታል መታወቂያ የሚሰጥ መሆኑም እንዲሁ።
የዲጂታል መታወቂያ ዋነኛ ጠቀሜታ ዜጎች በግልፅ መታወቅ በማስቻሉ ለአገሪቱ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ረቂቅ አዋጁ አስቀምጧል።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ለዜጎችና ለአገር ያለውን ጠቀሜታ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤