የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰሞነኛ ፕሮፖጋንዳ የአሸባሪውን ሕወሓት ሕልውና ለመታደግ ያለመ ጫና ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰሞነኛ ፕሮፖጋንዳ የአሸባሪውን ሕወሓት ሕልውና ለመታደግ ያለመ ጫና ነው
ጥቅምት 9/2015 /ኢዜአ/ የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰሞነኛ ፕሮፖጋንዳ ኢትዮጵያን ለማሽመድመድና የአሸባሪውን ሕወሃት ሕልውና ለመታደግ ያለመ ጫና መሆኑን አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ተናገሩ።
የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ውብአንተ አያሌው፤ በተለይም አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ ጥርሳቸውን የመንከሳቸው ሚስጢር ከአድዋ ድል መባቻ እንደጀመረ ያነሳሉ።
አገራቱ በየዘመኑ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ማዕቀብን ጨምሮ መልከ ብዙ ጫናዎችን ማድረጋቸውን በማውሳት፣ ዛሬም ከዚህ ፀረ- ኢትዮጵያ አቋም አዙሪት እንዳልተላቀቁ ይናገራሉ።
የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥም ለምዕራብ ኅያላን መንግስታት በቀጣናው ልዩ ፍላጎት እንዲኖራቸው በማድረጉ፣ ተሰሚነት የሌላትና የተዳከማች ኢትዮጵያ እንድትኖር ይሻሉ ብለዋል።
በመሆኑም አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት የአሸባሪውን ህልውና ለማስቀጠል የሚጥሩት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስደፈር በቀጣናው ላይ ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሁነኛ አጋር እንደሆናቸው ስለተረዱ ነው ባይ ናቸው።
የቻይና እና መሰሎቿ በቀጣናው የጀመሩትን የኢኮኖሚ አብዮት ተከትሎ በቀጣናው ያሳደሩት ተቀባይነት ሲያገኝ እና በፖለቲካ ሴራ የተተበተበው የምዕራብ አገራት ተቀባይነት ማጣትን ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ተዕጽኖ ፈጣሪነትና እንደ አፍሪካ ኢትዮጵያ ለምዕራባዊያን ራስ ምታት በመሆኗ፣ ሌላውን አፍሪካ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ኢትዮጵያን ህልውና ማናጋት አላማ አድርገው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ምዕራባዊያን ከሕወሓትና መሰል ባንዳዎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን በማዕቀብና ፖለቲካዊ ጫና ማሽመድመድና የተቀረውን አፍሪካ ደግሞ ለእነርሱ ገባር እንዲሆን ማድረግ ስልት እንደሆነ ገልጸዋል።
አሸባሪው ሕወሓት ባለፈው ዓመት ባደረግው ወረራ ወቅት የተደራደሩ ነጋሪት ሲጎስሙ እንደነበር አውስተው፤ በአንጻሩ ሕወሓት ሲመታ እያለቀሱ፣ ያሸነፈ ሲመስላቸው ደግሞ ጥፋቱን እያለባበሱ እንደቀጠሉ አብራርተዋል።
በዚህም ስውር ተልዕኳቸውን ለማሳካት እንዳሻቸው የሚዘውሯቸውን የአውሮፓና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመጠቀም አሸባሪውን ቡድን ለማትረፍ ጫናዎችን እንዳበረከቱ ገልጸዋል።
የእነዚህ ተቋማት ሰሞነኛ ጫናም አሸባሪውን በድን ለማትረፍና ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለማሽመድመድ ከመነጨ ፍላጎት እንደሆነ ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ሁሉም የዓለም ህዝብ ማገልገል ቢሆንም ተቋማቱ ግን በገሃድ ሃያላን መንግስታት ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንደሆኑ የተመድ መሪዎች ሰሞነኛ ቅስቀሳ ለማሳያነት አንስተዋል።
አሸባሪው ቡድን ከተመናመነ በአንጻሩ የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ከተጠናከረ አገራቱ ድብቅ ፖለቲካዊ ጨዋታቸውን ለማስፈጸም ይቸገራሉ ይላሉ ዶክተር ውብአንተ።
አገራቱ የሰብዓዊ ረድኤት ድርጅቶችን በመጠቀም የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሰፈጸም የገንዘብና ጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትም ይህን ሴራ ተረድቶ ከወዳጅ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማጎልበት አሸባሪውን ቡድን እስከመጨረሻው መደምሰስ ይገባቸዋል ብለዋል።