የ63 የፌዴራል መንግስት ተቋማት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ እየፈፀሙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ63 የፌዴራል መንግስት ተቋማት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ እየፈፀሙ ነው
ጥቅምት 09/2015(ኢዜአ) በተያዘው ዓመት የ63 የፌዴራል መንግስት ተቋማት የግዥ ሂደት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ እየተፈፀመ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ ጋር በመሆን ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ አተገባበር ላይ ምክክር አድርጓል።
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀጂ ኢብሳ፤ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ግዥን ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
ግዥውን ውጤታማ ለማድረግ የባለስልጣኑ የግዥ አዋጅና መመሪያ የማሻሻልና ሌሎች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ከ65 በመቶ በላይ የመንግስት በጀት ለመንግስት ግዥ የሚውል በመሆኑ ይህን ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ በሆነ አሰራር ለመምራት እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።
በኮንትራት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችና በወቅቱ ግዥ ያለመጸም፣ የዋጋ ንረትና ሌሎችም ችግሮች የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል የኤሌክትሮኒክስ ግዥ መፍትሄ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የግዥ ስርዓቱ በሚፈለገው ልክ ስራ ላይ እንዲውል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ግልጽ፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው ግዠ ለመፈጸም ባለስልጣኑ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው አጠናክሮ የሚቀጠል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወልደአብ ደምሴ በበኩላቸው ሲስተሙ ውጤታማ እንዲሆን የግሉ ዘርፍም መመዝገብ አለበት ብለዋል።
በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚደረጉ እንደ ኮንስትራክሽንና የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኦፕሬሽናል ስራ አስኪያጅ ዶይና ፔትሮስኩ፤ የኢትዮጵያ የመንግስት ግዥ ስርዓት እንዲዘመን ለማድረግ ባንኩ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የመንግስት ወጪ ውጤታማ እንዲሆንና በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ግዥ ተግባራዊ እንዲሆን የቴክኖሎጂና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንና ኮንትራክተሮች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ግርማ ሀብተማሪያም በበኩላቸው ለአገር ዕድገት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቀሰዋል።
በተለይ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለአገር ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ይህንኑ ለማሳለጥ ከመንግስትና ከአጋር አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።