ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የመንግሥት የሰላም እጆች አይታጠፉም- የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት

ጥቅምት 09/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የመንግሥት የሰላም እጆች መቼም ቢሆን አይታጠፉም ሲሉ  የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት የሰላም በሮችን ክፍት አድርጎ እየጠበቀ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት የዜጎቿ ትብብር፣ የሁሉም አካላት የሰላም ቁርጠኝነትና ለምክክር ዝግጁነት አስፈላጊ ነው።

በመሆኑም በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት የመንግሥት ቁርጠኝነት እንዳለ ቢሆንም በጥፋት መቀጠል ከፈለጉት አካላት ግን ተቃራኒ ሃሳቦች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ ከምንጊዜውም በላይ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የመንግሥት የሰላም እጆች አይታጠፉም ብለዋል።

በአንጻሩ መርህን ባልተከተለ አካሄድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ የውጭ ኃይሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በውስጥ ያሉ የሽብር ቡድኖችም በጥፋት እንቅስቃሴያቸው ቀጥለውበታል ነው ያሉት።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጋፋ ማንኛውንም እኩይ ዓላማን ይዞ ለሚንቀሳቀስ ኃይል መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የራስን ችግር በራስ የመፍታት ካልሆነም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንጂ ማደናቀፍ የለባቸውም ብለዋል።

አሸባሪው ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አጀንዳ አንግቦ አገር ለማፍረስ የቻለውን ሁሉ ጥረት ቢያደርግም በመንግሥትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት እየከሸፈ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም