የኢትዮጵያ የብሉ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ በዚህ አመት ይፋ ይደረጋል- የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብሉ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ በዚህ አመት ይፋ ይደረጋል- የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር
ጥቅምት 9/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የብሉ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ተሰርቶ በመጠናቀቁ በዚህ ዓመት ይፋ የሚደረግ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።
"ብሉ ኢኮኖሚ" የውቅያኖስ፣ የሐይቅና የባህር ሃብቶችን እንዲሁም ወደቦችን በዘላቂነት ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ የልማት ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል።
በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን በኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተቀርፆ መጠናቀቁን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ገልጸዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም የብሉ ኢኮኖሚ ልማት ውጤት እየተገኘበት ያለ መስክ መሆኑ ተመልክቷል።
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች 6 ሺህ 300 ባሕርተኞችን በውጭ አገራት ተቀጥረው ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ መደረጉን ሚንስትሯ ገልጸዋል።
በብሉ ኢኮኖሚ በማሪታይም የዓለምን ገበያ ለመቀላቀል ባለሙያዎችን በአገር ውስጥ በማሰልጠን በውጭ አገራት እንዲቀጠሩ በመደረጉ በዓመት አስከ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እየተገኘ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ ዘርፍ ከ100 ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚቻል የገለጹት ሚኒስትሯ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተሰርቶ መጠናቀቁን ገልጸው በዚህ ዓመት ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
የሎጂስቲክስ ሥርዓትን ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የማዘመን ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው በዚህም ይባክን የነበረን ጊዜና ገንዘብ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።
በዚህም እስካሁን 200 የሚጠጉ ኮንቴነሮችን ወደ ውጭ በመላክ አምራቾች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።
የአምራች ዘርፉን ትርፋማነትና ተወዳዳሪነት ለመጨመር የተጀመረው ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በነዳጅ ድጎማ፣ የውጭ ምርቶችን አሽጎ ከመላክ እንቅስቃሴ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሥራ ላይ ከማዋል አንፃር ውጤታማ ሥራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።