መንግስት የሰላምን አማራጭ እየተከተለ ሀገርን አደጋ ላይ በሚጥሉ ቡድኖች ላይም እርምጃ ሊወስድ ይገባል--የታሪክ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የሰላምን አማራጭ እየተከተለ ሀገርን አደጋ ላይ በሚጥሉ ቡድኖች ላይም እርምጃ ሊወስድ ይገባል--የታሪክ ምሁራን
ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥቅምት 9/2015 መንግስት በቀዳሚነት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ እየተከተለ የሀገርን ህልውና በሚፈታተኑና አደጋ ላይ በሚጥሉ ቡድኖች ላይ ግን ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ሲሉ የታሪክ ምሁራን ተናገሩ።
አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ህወሓትን በመደገፍ የኢትዮጵያን መንግስት ለማዳከም እየሰሩ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም ምሁራኑ ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ታሪክ ጥናቶችን በማድረግና ጥልቅ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በታሪክ መምህርነት ያገለገሉት አቶ አባቡ አሊጋዝ እንደተናገሩት፤ በዓለም ላይ ሰላምን ፍለጋ የተለያዩ ጦርነቶች ተደርገዋል።
"መጥፎ መንገድ ወደጥሩ ነገር ስለማያመራ" ሀገራት አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲያጋጥማቸው የሚገቡበት ጦርነት ጥሎ የሚያልፈው መጥፎ አሻራና ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።
ከዚህ ዓይነት ሁኔታ ለመውጣት በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ነው የገለጹት ምሁሩ።
የኢትዮጵያ መንግስትም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት ሰላምን ለማምጣትና የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት አሁንም የሰላም አማራጩን እንደሚገፋበት መግለጹን ያደነቁት መምህሩ፣ ለሰላም ከማንኛውም አካል ጋር መነጋገር ተገቢ ቢሆንም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ግን አሳስበዋል።
ምሁሩ እንደተናገሩት፤ ለሰላም ፍላጎት የሌለው ህወሓትና ጋላቢዎቹን ለማስታገስ ህዝብና መንግስት አንድነታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
የመንግስትን የሰላም አማራጭ ባለመቀበል የሀገርን ህልውና በሚፈታተኑና ሀገርን ለአደጋ በሚዳርጉ ቡድኖች ላይ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ገልጸዋል።
የታሪክ ምሁሩ እንዳሉት፤ በቀይ ባህርና በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ጂኦ ፖለቲካል እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሲሉ በቀጠናው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነችውንና ተሰሚነት ያላትን ኢትዮጵያ ለማዳከም የሽብር ቡድኑን በተለያየ መንገድ እየደገፉ ያሉ ሀገራት አሉ ብለዋል።
እነዚህ ሀገራት ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የአሻንጉሊት መንግስት መመስረት መሆኑን ተናግረዋል።
"በዚህም ህወሓት በጦርነቱ የገፋ መስሎ ሲታያቸው ዝምታን እየመረጡ የኢትዮጵያ መንግስት ለተከፈተበት ጦርነት ምላሽ ሲሰጥ ደግሞ የሰብአዊ መብት ጥሰትና መሰል ምክንያቶች እያነሱ ጫጫታ በመፍጠር ለቡድኑ ያላቸውን ድጋፍ በግልጽ እያሳዩ ነው" ብለዋል።
"ህወሓት ከመነሻውም ሰላምና ልማት የሚል ዕሳቤ የሌለው በሃይልና በጭፍለቃ የሚያምን፣ በትዕቢት የተወጠረ ቡድን ነው" ያሉት መምህር አባቡ፣ ቡድኑ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ለህዝብና ለሀገር ጠቃሚ አተያይ እንዳልነበረው ገልጸዋል።
ቡድኑ በትዕቢት በመወጠሩ የተነሳ ከእኛ በላይ ጦርነት አዋቂ የለም በሚል በየጊዜው በአደባባይ ጭምር ሲፈክር እንደነበር አስታውሰዋል።
"ይሁን እንጂ በሀገር ህልውና ጉዳይ መለያየትን ሆነ የትኛውንም የጠላት አጀንዳ የማይቀበሉት ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመነሳታቸው በተግባር የታየው ውጤት በተቃራኒው ሆኗል" ብለዋል።
"የሰላም አማራጮችን እየተጠቀሙ ለጉዳዩ መፍትሄ መስጠት ተገቢ ቢሆንም የህወሓት ባህሪ ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ ለእዚህም እርስ በርስ እንኳን አለመስማማታቸው አንድ ማሳያ ነው" ሲሉም ምሁሩ አክለዋል።
በውጭ ታሪካዊ ጠላት ድጋፍ ጦርነት ከፍቶ ዜጎችን እየዘረፈና እያወደመ አለሁ ለማለት ከሚሞክር ሽፍታና ቡድን ጋር መወያየት በራሱ የሞራል ልዕልና እንደማይፈቅደም አቶ አባቡ ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግስት ከሰላም ጥረቱ ጎን ለጎን በጀመረው ሀገርን የማዳን ተግባር የሽብር ቡድኑ እጅ እንዲሰጥ በማድረግ ለትግራይ ክልልም ሆነ ለኢትዮጵያ ሰላም መስራቱን እንዲያጠናከር አስገንዝበዋል
አንዳንድ ምዕራባዊያኑ ህወሓት እንዳከመና ዳግም ወደመንግስትነት እንደማይመጣ ሲረዱ ተኩስ አቁም ይደረግ ሲሉ መስተዋላቸውንም መምህር አባቡ ጠቁመዋል።
ሸንፈቱን ላለመቀበል እንወያይ የሚለው ህወሓት አቅሙን አሰባስቦ ጦርነት ሲከፍትና በንጹህን ላይ ጭምር ግፍና በደል እንዲሁም የጦር ወንጀል ሲፈጽም በዝምታ እንደሚያልፉ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የታሪክ መምህር በለጠ ሶጌቦ ናቸው።
መመህሩ እንዳሉት በቅርቡ የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የመክፈቻ ሥነስርአት ላይ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር ለመፍታት ማንኛውንም የሰላም አማራጭ እንደሚቀበል ማስቀመጡ ትክክለኛና ተገቢ ነው።
ይሁን እንጂ በህዝብ የተመረጠ ህጋዊ መንግስትና ላረቀቀው ህገ መንግስት እንካ ተገዥ ያልሆነው የሽብር ቡድን በእኩል መታየት እደሌለባቸው መምህር በለጠ አመልክተዋል።
ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መነጋገር አግባብ ቢሆንም የሰላም አማራጭን በማይቀበሉ ቡደኖች ላይ ግን መንግስት የጀመረውን የመከላከል እርምጃ በማጠናከር አደብ ሊያሲዛቸው እንደሚገባም የታሪክ መምህሩ ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት ተጨማሪ ጦርነት መክፈት የሚችልበት እድል እንዳያገኝና ሰላም፣ ልማትና ሀገራዊ አንድነትን በዘላቂነት ለማምጣት ህዝብና መንግስት በቅንጅት መስራታቸውን እንዲያጠናክሩም መክረዋል
የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማጠናከር የዲፕሎማሲ ስራ በኤምባሲዎች በኩል ከመስራት ባሻገር ህብረተሰቡ የሚሳተፍባቸውን ንቅናቄዎች መፍጠርም ተገቢ መሆኑን መምህር በለጠ ጠቁመዋል።
የታሪክ ምሁራኑ እንዳሉት ሰላምን ሁሌም እንደቀዳሚ አማራጭ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ከአሸባሪ ህወሓት ባህሪ አንጻር እርምጃ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ መወሰን ሀገርን ከተጨማሪ ጥፋት ይታደጋል።