ቀጥታ፡

በክልሉ ከመኸር እርሻው 86 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል - ቢሮው

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 9 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ከመኸር እርሻው እንቅስቃሴ 86 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል  ግብርና ቢሮ  ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው በ2014/2015 የምርት ዘመን በሁሉም የአዝርዕት ከለማው 1 ሚሊዮን 187 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ  ላይ ነው።

በምርት ዘመኑ 1 ሚሊዮን 250 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 96 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ  በየደረጃው ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን ሃላፊው አስታውሰዋል።

ሆኖም በክልሉ ጎፋ፣ ቡርጂ፣ ኮንሶ፣ አሌና  ጋሞ  የተወሰኑ  አካባቢዎች  የመኸር  ዝናብ  የመቆራረጥ ችግር በማጋጠሙ በዘር ለመፈሸን ከታቀደው መሬት ውስጥ 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን አመላክተዋል።  

የምርት ዘመኑ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በክረምቱ መጠቀም በመቻሉ እና የዝናብ ሁኔታውም ጥሩ የሚባል በመሆኑ ሰብሉ በተሻለ  ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዋና ዋና ሰብሎች የለማው ምርት ሲታይም የአገዳ፣ የብርዕ፣ የጥራጥሬ እና የቅባት ሰብሎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ጠቅሰዋል።

በክልሉ በዋናነት የሚመረቱ ሰብሎች ከሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ባለፈ ለኢንዱስትሪ  ግብዓትና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አውሰተዋል።

የመኸሩ አዝመራ በክልሉ በበልግ ወቅት በዝናብ እጥረት የታየውን የምርት መቀነስ ሊያካክስ በሚችል መልኩ ሰፊ ርብርብ መደረጉን  አስታውሰው፤ እንደ  ክልሉ ከለማው መሬትም ከ86 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

ከሚሰበሰበው ምርት ውስጥ ከ98 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው  ለቀጣይ ሰብል ልማት የሚውል ምርጥ ዘር መሆኑን በመጠቆም።

በመኸር እርሻው ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል በሀላባ ዞን ወይራ ዲጆ ወረዳ ኢንሾክር ቀበሌ ነዋሪ ሎራጎ ኡላላ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት  ኑሯቸውን በግብርና ሥራ እንደሚመሩ ገልጸው በመኸር አዝመራው በቆሎ፣ስንዴ፣ቦለቄ፣ዳጉሳና ገብስ ማልማታቸውን ተናግረዋል።

 አሁን ላይ ሰብሉ በመልካም ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተለይ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት ልማቱን በኩታ ገጠም ጭምር በማካሄዳቸው ከ480 ኩንታል በላይ የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

በወረዳው በዘመናዊ ግብርና ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል የፋሪስ አብደላ እርሻ ልማት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ፋሪስ አብደላ እንዳሉት በ2014/2015 የምርት ዘመን በ170 ሄክታር ስንዴና በ20 ሄክታር ደግሞ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ብዜቱን ከደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት የቴክኒክ ድጋፍ በመታገዝ  እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመው ከልማት እንቅስቃሴውም በሄክታር 30 እስከ 50 ኩንታል ስንዴና የበቆሎ ምርት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

በቅርቡ ወደ ምርት መሰብሰብ ተግባር እንደሚገቡ ገልጸው በቀጣይም አምና በ17 ሄክታር የጀመሩትን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዚህ ዓመት ወደ 40 ሄክታር ለማሳደግ ማቀዳቸውን አውሰተዋል።

እርሻ ልማታቸው በዘር ብዜት ስራ ከተሰማራ 10 ዓመት ማስቆጠሩንና አሁን ላይ ካፒታሉን ከ2 ሚሊዮን  ወደ 25 ሚሊዮን  ብር ማሳደግ መቻላቸውንም አብራርተዋል።

በአካባቢው አራት ቀበሌዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዘመናዊ የአሰራር ክህሎት በመስጠት ድጋፍ ከማድረጋቸው ባሻገር እርሻ ልማቱ ለ150 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በድርጅቱ እና በግል ባለሀብቶች ቅንጅት በሀላባ ዞን ወይራ ዲጆ ወረዳ በ910 ሄክታር መሬት ላይ የለማውን የስንዴ ምርጥ ዘር ማሳ በቅርቡ መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም