መንታ ምጥ...

111

በሀብታሙ ገዜ (ከጅግጅጋ ኢዜአ)

ይህን ገጠመኝ አለመፃፍ "ክስተቶችን በብዕሬ ከትቤ ለሕዝብ አደርሳለሁ፣ አሳውቃለሁ፣ አስተምራለሁ፤ ሰንጄ  የታሪክ ድርሳንን በማህደር አኖራለሁ፤ እዘግባለሁ፤ እፅፋለሁ"  ላለ ሰው ያውም እንደ እኔ በጋዜጠኝነት ሙያ ለተሰማራ ሙያተኛ ፍፁም ስህተት ይሆናል ብዬ አሰብኩ፤ እናም ያየሁትን ክስተት በዚህ መልኩ ጻፍኩት።

ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ በ615 ኪሎ ሜትር ርቀት ትገኛለች የሶማሌ ብሄራዊ ከልላዊ መንግሥት  ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ። ከጅግጅጋ በስተምስራቅ ደግሞ በ380 ኪሎ ሜትር ርቀት በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ሥራዋ የሚያሳብቀው በረሃማዋ የቀብሪደሃር ከተማ ትገኛለች። ከጠረፍ ከተሞች የምትመደበው የጎዴ ከተማ ደግሞ ከቀብሪደሃር በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አምሮባት ትታያለች። ዕድሜ ጠገቧ ጎዴ በሚገባት ደረጃ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ግን ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል።

የአየሩ ሙቀቱ ይንቀለቀላል፤ ግለቱ አይጣል ነው። ይህ  ተፈጥሯዊ  ሙቀትና ሐሩር  ለእንደኔ ዓይነቱ አዲስ ሰው እንጂ ለአካባቢው ነዋሪ የተለመደ ነው።

ቀለል ያለ ድሪያ የለበሰችና አናቷን ከድሪዋ ስምሙ(ማች የሚያደርግ) በሆነ ፎጣ ጸጉሯን ና ፊቷን ተከናንባ መኪና ውስጥ ገባች። ሁለንተናዋ የሚያሳሳ ቀጭን ቁመተ ለግላጋ መለሎዋ ወጣት ከጎዴ ከተማ ሰባት ኪሎ ሜትር ተጓጉዛ ቀብሪደሃር ዩኒቨርስቲ ደርሳለች። በዩኒቨርስቲው የተከሰተችው ዘንድሮ ኩረጃና ስርቆትን ለማስቀረት በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ያለውን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የመጀመሪያውን ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ለመውሰድ ነው። በለበሰችው ድሪያ ጅቡን፤ ጅቡንቡን አድረጋ ሸሽጋ! የያዘችው አንዳች ሚስጥር ስለመኖሩ ግን የተጠራጠረ የለም፤ተከትለዋት ከመጡት ከእናቷ (ሆዬ) እና ከእህቷ በስተቀር።

በመጀመሪያው  ዙር በማህበራዊ ሳይንስ  ዘርፍ የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና  በብዙ አስደናቂ  ክስተቶች የተሞላ ነበር። በማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች በተጀመረው ፈተና ላይ የነፍሰ ጡርና የወለዱ ተማሪዎች የዓላማ ፅናት፣ የአዛውንት አባቶች ከልጆቻቸው ጋር በፈተናው ላይ መቀመጥና ለአዲሱ ትውልድ አርዓያ መሆን፣ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እልህ አስጨራሽ ትግል፣ ሌላም ሌላም በማህበረሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮችን ትቶ ያለፈ ክስተት ነው፤ በማህበራዊ ሳይንስ  ዘርፍ የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና።

ወደ ዋናው ትርክቴ ተመልሻለሁ፤ የ19 አመቷ ለግለጋዋ ተፈታኝ ወጣት ኡባህ  አብዲ የጎዴን በረሃ አቋርጣ ቀብሪደሃር ዩኒቨርስቲ ለፈተና እስክትቀመጥ ድርስ ነፍሰጡር መሆኗን የተጠራጠረ አንድም ሰው አልነበረም። ነገር ግን በማህበራዊ ሳይንስ  ዘርፍ የተሰጠው የመጀመሪያውን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና  የመጀመሪያውን የፈተና ገፅ እንደገለጠች አንዳች እፎይታ የሚነሳ ቁርጠት ያምሳት ጀመር። በማህፀኗ ውስጥ የሚላወሰው ሽል እፎይታ ነሳት፤ እያረጋገጠ፤ "እናቴ ወደ አዲሱ ዓለም ልውጣ" የሚለውን  ዜማ  በእትብቷ  የማዳመጫ መስመር እያንቆረቆረላት ነበር። አእምሮዋ እና አይኖቿ በተገለጠው የፈተና ጥያቄዎች እና በማህፀኗ እፎይታ በነሳት ቁርጠት ይተራመሳሉ። በመስቀለኛ መንታ የምጥ ጭንቀት የተወጠረችው ኡባህ የአቃተኝ የድረሱልኝ፤  እሪታዋን አስተጋባች።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በጊቢው ውስጥ  ስንዱ የሆነው አንቡላንስ ፈጥኖ ቀብሪደሃር ጠቅላላ ሆስፒታል አደረሳት። "እፈተናለሁ፤ የፈተና ወረቀቴን ተሸክሜ ነው የምሄደው " ባለችው መሠረት ፈታኝ ከነአጃቢ የፀጥታ አካል ጋር ተያይዘው ወደ ሆስፒታሉ አብረው ተጓዙ።

እኔም በሥራዬ ምክንያት በቦታው ነበርኩና አንድም ሙያዬ የሰጠኝ ማህበራዊ ኃላፊነት ሁለትም ሰብዓዊነት ያስገድዱኛልና አብሬ ወደ ሆስፒታሉ ተጉዤ ኡባህን፣ ታላቅ እህቷን ሃምዳን እና እናቷን ወይዘሮ አርዶ አብዲን ለማነጋገር ሞክርኩ። ተፈታኟ ኡባህ በሆስፒታሉ አንድ ክፍል ውስጥ የፈተና ወረቀት ላይ ተመስጣ እያቀለመች ነው፤ በተመሣሣይ ደቂቃዎች በማህፀኗ ያለው ሽል እየተገላበጠ እፎይታ እየነሳት ነው። የፅናት ፣ የሴቶች ቆራጥነት ዳር መንገድ ማሳያ አንዷ ተምሳሌት መሆኗን አረጋገጥኩኝ።

የተመደበላት ፈታኝ የትምህረት ሚኒስቴር በሰጣት ዕድል ተጠቅማ አንዱን ተፈጥሯዊውን የእናትነት ልዩ ፀጋ የትውልድ ቀጣይነት ማረጋጋገጫ ምጥን ብቻ እንድታስተናግድ ያላደረገው ጥረት አልነበረም። "ወላሂ፤ ይሄን ሁሉ በረሃ አቋርጬ እዚህ የመጣሁት እየወለድኩም ቢሆን ፈተናዬን ለመጨረስ ነው" የሚል ምላሽ ነበር በምትንከባከባት የጤና ባለሙያ በኩል የመለሰችው።

ባይሳካላቸውም ቅሉ የሚፈትኗት መምህር "ለዓላማዋ ስኬት እስከመጨረሻው ያሳየችው ፅናት ለሁላችንም ምሳሌ ነው፤ ሁላችንም በየተሰማራንበት ሙያ መስክ በዚህ መንገድ ከተጓዝን የማይመጣ ለውጥ አይኖርም" ሲሉ ነው የኡባህን የዓላማ ፅናት ተምሳሌትነት የገለጹልኝ። ጠይሟ  ወላጅ እናቷ (ሆዬ የሶማልኛ ትርጉም) ዓይናቸውን በስስት በልጃቸው ላይ ከማንከራተት በስተቀር  የሚተነፍሱት አንዳች ቃል አልነበረም።

እናም ወደ ታላቅ  እህቷ  ወጣት ሃምዳ አቀናሁ፤ በትህትናም ሰላምታ አቀረብኩላትና ራሴን አስተዋወኩ።እሷም የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ በሆነው በጥሩ ትህትና ከፈገግታ ጋር ተቀብላ አወጋችኝ፤ በጉራማይሌ ውብ ቋንቋ። በሶማራ_በሶማልኛ እና በአማርኛ ብዬዋለሁ፣ ቅይጡን (ጉራማይለውን) ቋንቋ። "ኤግ (ስማ) ኢሷ ኢኔ ቢኖር መንጊሥቲ ኢድሉ ይጠቅማል፣ ኡባህ ኢንቢ አለ" አለችኝ፤ ፊቷ ላይ በስሱ የኃዘን ድባብ አርብቦባታል። በመነፅር  የተከለሉት ዓይኖቿ እንባ አቅርረዋል። የእህቷ ቁርጠኝነት በተለይ ለመጪዎቹ አዳጊ ሴቶች በዓላማ ፅናት በብዙ መንገድ አርዓያ መሆኗን  ገልጬ  ልለያት ስል፤ "መሃይ...ዋሃ አድ ኢ ዳሃዳይ ማ ሃፋሃሚን...." ስትል  ሌሎች ሃሳቦቿን በአፍ መፍቻ ቋንቋዋ ተነፈሰች። ያልኩት እንዳልገባት ሁሉ ያለችውንም በጨረፍታ ነው የገባኝ። ቱርጁማን ጠርተን ተግባባን። አመስግኜ ተለየዋት።

ሆስፒታሉን ለቅቄ በቅርበት ወደ ሚገኘው የቀብሪደሃር ዩኒቨርስቲ ለመጓዝ ባጃጅ ያዝኩ። ከዩኒቨርስቲው እንደደረስኩም የቀብሪደሃር ዩኒቨርስቲ የፈተና ግብረ ኃይል አሰተባባሪ አቶ ሲፋኒ ብርሃኑን አገኘዋቸሁ። ኡባህ መንግሥት ያመቻቸውን አማራጭ ዕድል እንድትጠቀም መክረናት ነበር፤ በፍፁም ልትቀበለው አልፈለገችም፤ መብቷን ማክበርና መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ ፈታኝ እና ተቆጣጣሪ የጥበቃ አባል መድበን ፈተናውን እንድትፈተን አድርገናል ሲሉ ነው ክስተቱን፣ የኡባህን አይበገሬነትና  የዓላማ ፅናት የገለጹልኝ።

የኡባህ  መንታ ምጥ፤ የዓላማ ፅናት በቀብሪደሃር ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያው  ዙር በማህበራዊ ሳይንስ  ዘርፍ የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ልዩ ክስተት፤ ከመሆኑም ባሻገር  የሴቶችን የፅናት ጥግ፣ የፅናት መዳረሻ፣ አንዱ ማሳያ ተምሳሌት በመሆኑ ሁሌም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም